አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር ወደ ግጭት በገባችበት የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በተለይም የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት በዓለም የንግድ እንቅስቃሴና ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሮ ቆይቷል፡፡
የሰርጡ መዘጋት በተለይም በነዳጅና ሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ በፈጠረው መስተጓጎል በተለይም በመሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ ዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት አስከትሏል፡፡
እንደ ሆርሙዝና ባብ ኤል ሜንደብ ያሉ የዓለም ቁልፍ የንግድ መተላለፊያ መስመሮች ደህንነት የአካባቢው ሀገራት ብቻ ሳይሆን፤ የዓለም ጉዳይ ለመሆኑ ይህ አስረጂ ክስተት ነው፡፡
የየመኑ ታጣቂ ቡድን ሁቲ በቀይ ባህር ቀጣና በባብ ኤል ሜንደብ የንግድ መተላለፊያ መስመር ላይ እያደረገው ያለው እንቅስቃሴ መሰል ውጤት እንዳያስከትል ተሰግቷል፡፡
ሀያላን ሀገራት በቀይ ባህር ቀጣና መልሕቃቸውን ለመጣልና የጦር ሰፈር ለመገንባት ውቅያኖስ አቋርጠው የመጡበትን ገፊ ምክንያት ስናጤን የአካባቢው ደህንነት ምን ያህል ወሳኝ መሆኑ እንገነዘባለን፡፡
በቀጣናው ያንዣበበው አደጋ ከቀይ ባህር በ60 ኪሎ ሜትሮች ገደማ ቅርብ ርቀት ላይ ለምትገኘው ኢትዮጵያ ጠንከር ያለ መልዕክት ያስተላልፋል፡፡
ሁኔታው ለኢትዮጵያ እና ለቀጣናው ሀገራት ጉልህ የማንቂያ ደወል ነው፤ ከዚህም ባሻገር ቀጣናው እንደ ኢትዮጵያ ያለ ጠንካራ ወታደራዊ አቅም ያለውን ሀገር ይሻል፡፡
መቀመጫውን በእንግሊዝ ለንደን ያደረገው ዓለም አቀፉ የጥናትና ምርምር ተቋም ቻንተም ሀውስ እንደሚለው፤ ሁቲዎች በቅርብ ጊዜያት እንቅስቃሴያቸው በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ደህንነት ላይ ጭምር ጫና አሳድረዋል፡፡
የጥናት ቡድኑ ባሳለፍነው ሰኞ ባስነበበው ሰፋ ያለ ሀተታ፤ ቡድኑ በዓለም የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ፣ በኢነርጂ ገበያ እንዲሁም በባህረ ሰላጤው እና በአፍሪካ ቀንድ ተጽዕኖ መፍጠር መቻሉን ያስረዳል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ የቀይ ባህር ቀጣና በተለይም ደግሞ የባብ ኤል ሜንደብ ደህንነት ከቀይ ባህርና ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጥቅም ጋር ስትራቴጂያዊ ቁርኝት እንዳለው አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
እነዚህ እውነታዎች የሚያረጋግጡት እንድ እውነት፤ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ደህንነት መናጋት ተጽዕኖ የሚያሳድርባት በመሆኑ ከቀጣናው ደህንነት አጀንዳ ተገልላ መቀጠል እንደማትችል ነው፡፡
ይህም ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ቀጥተኛ የባህር በር ማግኘት እንደሚገባት ብቻ ሳይሆን፤ ለጠቅላላው የቀጣናው ደህንነት ኢትዮጵያ አስፈላጊ መሆኗን በግልጽ ያመላክታል፡፡
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና ደኅንነትን ለማስጠበቅ እንደ አልሸባብ ያሉ አሸባሪ ቡድኖችን በመዋጋት ቁልፍ ሚና ተጫውታለች፡፡
አሁን ላይ የገነባችው ወታደራዊ አቅምና የቀጣናውን ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ያለፈችበት ልምድ ለቀይ ባህር ቀጣና ሰላምና ደህንነት አስፈላጊ አድርጓታል፡፡
ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የቀጣናው ሰላም ለሚገዳቸው ሁሉ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ያሉት፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

