አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ መንግሥት ከስፖርት ውርርድና ሎተሪ ዘርፍ ማግኘት የነበረበትን 27 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ አጥቷል አለ የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት፡፡
የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት በሀገሪቱ የስፖርት ውርርድና ሎተሪ ዘርፍ ላይ ባካሄደው ገለልተኛ ምርመራ÷ፈቃድ ያላቸው ኦፕሬተሮች በኮሚሽን፣ በቅጣት፣ በፈቃድ እድሳትና ለምዝገባ መክፈል የሚጠብቅባቸውን ግዴታ አለመወጣታቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
በዚህም ምክንያት መንግሥት በኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት በኩል ማግኘት የነበረበትን 27 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ እስካሁን አለማግኘቱ ነው የተገለጸው፡፡
ረቂቅ የኦዲት ሪፖርቱ የስፖርት ውርርድ እና ሎተሪ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ፈቃድ ካገኙበት ሐምሌ 2015 ዓ.ም ፈቃዳቸው እስከታገደበት ታሕሳስ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ያሉትን አራት ዓመታት የሸፈነ ነው።
በእነዚህ አራት ዓመታት ውስጥ ብቻ በስፖርት ውርርድ እና ሎተሪ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች 199 ቢሊየን ብር ማንቀሳቀሳቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
ድርጅቶቹ በአራቱ ዓመታት ውስጥ ካንቀሳቀሱት ገንዘብ ላይ በኮሚሽን ብቻ ለመንግስት 30 ቢሊየን ብር መክፈል ሲገባቸው የከፈሉት 3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ብቻ ሲሆን ÷ በዚህም መንግሥት እና የብሄራዊ ሎተሪ አገልግሎቱ ከ27 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አጥተዋል።
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ለብሄራዊ ሎተሪ አገልግሎት መከፈል ከሚገባው 27 ቢሊየን ብር ውስጥ 32 በመቶ ማለትም 8 ነጥብ 64 ቢሊየን ብር ዳሽ ቤቲንግ በተባለ በአንድ ድርጅት ላይ ተከማችቶ ይገኛል።
ቀሪ 19 ቢሊየን ብር ደግሞ ከአስር ድርጅቶች የሚጠበቅ እና እስካሁን ያልተከፈለ ክፍያ መሆኑ በኦዲት መረጋገጡ ተጠቅሷል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ሎተሪ አስተዳዳር ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ቤዛ ግርማ ÷ መረጃው ትክክል መሆኑን አረጋግጠው፤ ምርመራው የዘርፉን ሁኔታ በማስረጃ ለመረዳትና ቀጣይ የለውጥ ሥራዎችን ለመምራት ሲባል የተከናወነ ነው ብለዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አገልግሎቱ ሰፊ ተቋማዊ ሪፎርም ላይ መሆኑን ጠቁመው ÷ የተከማቸው ክፍያ በኦዲት ከተለየ በኋላ ገንዘቡን የማስከፈል ርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመተባበር 27 ቢሊየን ብሩን ከድርጅቶቹ ለመሰብሰብ የትኛውንም ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል።
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያደረገው ምርመራ እንደሚያመለክተው ÷ የስፖርት ውርርድ በመንግሥት ውሳኔ ባላፈው ዓመት ታሕሳስ ወር ላይ የታደገ እና ድርጅቶችም ፈቃዳቸው የታገደ ቢሆንም፤ ውርርዱ ግን አሁንም በህገ ወጥ መንገድ ቀጥሏል።
በመስኩ የሚዘዋወረው ገንዘብም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቶ በ2018 ዓ.ም መስከረም ወር ብቻ 20 ቢሊየን ብር ተንቀሳቅሶበታል፤ይህም በ2015 ዓ.ም አስራ ሁለት ወራት ከተንቀሳቀሰው 4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በአራት እጥፍ ይበልጣል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ባለፈው ዓመት የታገደውን የስፖርት ውርርድ ከመተግበር አንጻር የመንግሥት አቅጣጫው በዘርፉ ተጠያቂነትን ማስፈን መሆኑን አመልክተዋል፡፡
አገልግሎቱ የመጨረሻውን የኦዲት ሪፖርት እንደተቀበለ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመቀናጀት የተለዩትን የገንዘብ ግዴታዎች የማስመለስ ሥራ እንደሚያከናውን ጠቁመዋል፡፡
የቁጥጥር ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ ለማጠናከርም የኦፕሬተሮች የፋይናንስና የሕግ ግዴታዎች በአንድ ወጥ ዲጂታል ሥርዓት እንዲመዘገቡና እንዲተከታተሉ ለማድረግ መሰራቱን አብራርተዋል፡፡
የውል ስምምነቶችን ማቋረጥና ፈቃዶችን መሰረዝ ጋር ተያይዞ ከ100 ቢሊየን ብር በላይ የተደበቀ ገቢን በተመለከተ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የተካሄደውን ምርመራ ተከትሎ የስፖርት ውርርድ ፈቃዶች የተሰረዙ ሲሆን÷ ያልተሟሉ የውል አፈጻጸሞች በመኖራቸውም ከዲጂታል ሎተሪ ጋር የተያያዘው የግል አጋርነት ስምምነት ተቋርጧል ብለዋል።
ይህ አጠቃላይ የሪፎርም እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽን 2030 ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ ሲሆን÷ በኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ቦርድና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገለት እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
የመንግሥት ዋና አቅጣጫ የመንግሥትን ገቢ ማስከበር፣ የተጫዋቾችን መብት ማስጠበቅና ዘርፉን በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ ማድረግ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የስፖርት ውርርድና የዲጂታል ሎተሪ አገልግሎቶች በጠንካራ ቁጥጥርና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘው በአዲስ መልክ እንደገና እንዲጀምሩ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል፡፡
መንግሥት ከስፖርት ውርርድና ሎተሪ 27 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ አጣ

