አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የቺሊ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሚቼል ባችሌት ከተባበሩት መንግስታት ዋና ጸኃፊ ዕጩ ተወዳዳሪነት ራሳቸውን አግልለዋል፡፡
የመጀመሪያዋ የተባበሩት መንግስታት ሴት ዋና ጸኃፊ ለመሆን የሚያስችላቸውን ውድድር ያቋረጡት ከጸጥታው ምክር ቤት የጠበቁትን ያህል ድጋፍ ባለማግኘታቸው ነው ተብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ባለፈው አርብ ባካሄደው መደበኛ ያልሆነ የድጋፍ ድምፅ አሰጣጥ ስነ ስርዓት የ74 ዓመቷ አዛውንት ያገኙት አንድ የማበረታቻ ድምፅ ብቻ ሲሆን ተፎካካሪዎቻቸው የኮስታ ሪካዋ ርብቃ ግራይንስፓን ዘጠኝ እንዲሁም የጉያናዋ ካሮላይን ሮድሪጌት ብሪኬት ስምንት የምክር ቤቱን የድጋፍ ድምፅ አግኝተዋል፡፡
በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2017 ጀምሮ ተቋሙን ሲመሩት የነበሩት አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ለመተካት ከሚወዳደሩት መካከል የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ተቆጣጣሪ ድርጅት ዋና ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ፣ የሴኔጋል የቀድሞው ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል እንዲሁም ኢኳዶራዊቷ ዲፕሎማት ማሪያ ፈርናንዳ እስፒኖሳ እንደሚገኙበት አልጃዚራ ዘግቧል፡፡
በጸጥታው ምክር ቤት ድጋፍ ለማግኘት ከካውንስሉ 15 አባላት ሀገራት ውስጥ ቢያንስ የዘጠኑን ድጋፍ ማግኘት እና ከየትኛውም ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ካላቸው ሀገራት ተቃውሞ ካልገጠማቸው ብቻ ነው፡፡
ይህን ላሟሉ ዕጩች የጸጥታው ምክር ቤት ምክረ ሃሳብ ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀርባል፡፡
የምክረ ሃሳቡን ተቀብሎ የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ዋና ጸሐፊውን በድምፅ ይመርጣል፡፡
ሁለቱ አፍሪካዊያን ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊን እና ኮፊ አናንን ጨምሮ የተባበሩት መንግስታትን በ80 ዓመታት ዕድሜው ውስጥ ዘጠኝ ዋና ጸሐፊዎች ተፈራርቀው መርተውታል፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ

