አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የቦሮ ሽናሻ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ጋሪ ዎሮ” በዓል በአዲስ አበባ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል፡፡
በአከባበር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ም/ቤት አፈ ጉባዔ አስካለች አልቦሮ ÷ የጋሪ ዎሮ በዓል የሽናሻ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን የይቅርታ፣ የአብሮነት፣ የሰላምና የተስፋ በዓል መሆኑን አውስተዋል፡፡
የብሔረሰቡን ባህላዊ እሴቶች የበለጠ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አፈ ጉባዔዋ ÷ ለዚህም በአሶሳ ከተማ የባህል ማዕከል ግንባታ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ተወካይ ከፍያለው አብዲሳ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ የሚገኙ የብዝሃ ባሕል ሃብቶችን በማልማት ለሀገር ልማት እንዲውሉ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
የቦሮ ሽናሻ ብሔረሰብ የማንነት መገለጫ የሆነው ጋሪ ዎሮ ትልቅ የአብሮነት መድረክ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው ÷ በዓሉን ይበልጥ ለማልማትና ለማስተዋወቅ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በበዓል አከባበሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ባሕላዊ አልባሳትን፣ ባህላዊ ውዝዋዜዎችንና የምግብ አይነቶችን እንዲሁም የተለያዩ ትርዒቶችን አቅርበዋል፡
የዘንድሮው የጋሪ ዎሮ በዓል ከመስከረም 16 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም በክልል ደረጃ በአሶሳ ከተማ ባሕላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል።
በጀማል አሕመድ

