አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስመዘገበችው ውጤት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ ምሳሌ እንደሚሆን ተመላክቷል።
በአፍሪካ ዘላቂ የስንዴ ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን፣ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋትና ብሔራዊ የዘር ሥርዓቶችን ማጠናከር ላይ ያተኮረ አህጉራዊ ዓውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በአህጉራዊ ዓውደ ጥናቱ ላይ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ያሳካችው ውጤት አድናቆትን ያተረፈ ሲሆን÷ በዘርፉ የተገኘው እመርታ ለአፍሪካ ሀገራት አርአያ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
መርሐ ግብሩን የዓለም አቀፍ ደረቅ ቦታዎች የግብርና ምርምር ማዕከል ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ከአፍሪካ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎችና ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጀው።
በመድረኩ ላይ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የዘር ኩባንያዎች፣ ተቆጣጣሪ አካላት፣ የአርሶ አደር ማህበራት እና የልማት አጋሮች ተሳትፈዋል።
አሁን ላይም በስንዴ ምርት ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችን ለመገምገም እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመለየት ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
በዓውደ ጥናቱ በዘርፉ ጥራት ያለው ዘር የማግኘት ውስንነትና ሌሎች ተግዳሮቶችን መፍታት የሚያስችሉ አማራጭ ሃሳቦች ይመላከታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በታሪኩ ለገሰ

