Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ከፍታ፡ በመደመር መንግሥት የተመዘገቡ አስደናቂ ስኬቶች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ዘርፎች የታየው የሽግግር ጉዞ በዋናነት በመደመር ፍልስፍና የተቃኘ ነው፡፡
የመደመር መንግሥት እሳቤ ያለፉትን አዎንታዊ እሴቶች በማስቀጠል፣ ስህተቶችን በማረም እና የነገዋን ኢትዮጵያ ብሩህ ለማድረግ አዳዲስ እይታዎችንና አሰራሮችን ማካተት ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ይህ አስተሳሰብ ወደ ተግባር ሲቀየር በሀገሪቱ የልማት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚይዙ፣ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያረጋግጡ ግዙፍ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በመደመር መንግሥት ከተከናወኑት አበይት ተግባራት መካከል አንዱ ለዓመታት ተጀምረው ሳይጠናቀቁ የቆዩ ወይም የታቀዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ወደ ፍፃሜ ማድረስ እና አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን መገንባትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት ውጤትና የሉዓላዊነት ምልክት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ከነበረበት አዘቅት ውስጥ በማውጣት የውሃ ሙሌትና የኃይል ማመንጨት ምዕራፎችን አከናውኖ ማጠናቀቅ የተቻለው በዚሁ ከለውጡ በኃላ በመጣው የመደመር መንግሥት ነው፡፡
ሀገሪቱ ያላትን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ፀጋዎች ወደ ኢኮኖሚ ሀብት ለመቀየር በወንጪ፣ ጎርጎራ፣ ኮይሻ እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተገነቡት የኤኮ-ቱሪዝም ፕሮጀክቶች የሀገር ውስጥና የውጭ የቱሪዝም ፍሰትን በእጅጉ አነቃቅተዋል።
በመዲናዋ አዲስ አበባ እና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ፣ ጽዱና ዘመናዊ በማድረግ ልዩ ውበት አጎናጽፏቸዋል፡፡ በዚህም የበርካታ ከተሞች ገጽታ ከመቀየሩ ባለፈ ለኢኮኖሚም ከፍተኛ አበርክቶን በመለገስ ላይ ይገኛል፡፡
የአፍሪካን የአቪዬሽን ገበያ በግንባር ቀደምትነት የሚመራው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ አዲስ በመገንባት ላይ ያለው የአውሮፕላን ማረፊያ፤ ሀገሪቱ ታላቅ ትልሞችን ወደ ተግባር ማውረድና መፈጸም እንደምትችል ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የቻለችና ከሀገር ፍጆታ አልፎ ኤክስፖርት የምታደርግ ሀገር ለማድረግ በግብርናው ዘርፍ መሠረታዊ የፖሊሲና የተግባር ለውጥ ተደርጓል።
ከዚህ ቀደም ሙሉ በሙሉ ከውጭ ይገባ የነበረውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ መተካት ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ውጭ ሀገራት መላክ የተጀመረበት ታሪካዊ ስኬት ተመዝግቧል። ይህ ርምጃም ሀገሪቱ የምግብ ሉዓላዊነቷን እንድታረጋግጥ ትልቅ መሠረት ጥሏል።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና አፈርን ከመሸርሸር ለመታደግ በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞች ተተክለዋል። ይህ የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ ኢትዮጵያን በአካባቢ ጥበቃ ረገድ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ አርአያ ያደረገ ግዙፍ ህዝባዊ ዐሻራ ነው።
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ ወደተደገፈ ሥርዓት ለመቀየር “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂ ተተግብሮ በስኬት በመጠናቀቅ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ወደ ተግባር ተገብቷል።
በዚህም ለዘመናት በአንድ የመንግሥት ተቋም ብቻ ይመራ የነበረውን የቴሌኮም ዘርፍ ለውድድር ክፍት በመደረጉ አገልግሎቱ እንዲስፋፋና እንዲዘምን አድርጓል።
የዲጂታል የክፍያ ሥርዓቶች መስፋፋት የፋይናንስ አካታችነትን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን፣ የጥሬ ገንዘብ ንክኪን በመቀነስ የንግድ እንቅስቃሴውን እጅግ ቀልጣፋ አድርጎታል።
በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያ ያላትን ተደማጭነት እና ተፅዕኖ ለማሳደግ በዲፕሎማሲው መስክ የተሰሩ ሥራዎች አስደናቂ ውጤት አስመዝግበዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ታላቁ የትብብር ማዕከል የሆነው የብሪክስ ስብስብ አባል መሆን ችላለች። ይህም ለኢኮኖሚ፣ ለኢንቨስትመንት እና ለዲፕሎማሲያዊ ከፍታ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
በአፍሪካ ህብረት እና በዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ድምፅ የማሰማት እና የሰላም ግንባታ ጥረቶችን የመምራት ሚናዋን አጠናክራ ቀጥላለች።
በአጠቃላይ በመደመር መንግሥት የተከናወኑት ግዙፍ ሥራዎች ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ከፍታዋን እንድትቆናጠጥ መሰረትን የጣሉ እንዲሁም ለወደፊቱ ትውልድ ጠንካራ ሀገር ለማሻገር ያለንን ተስፋ እያለመለሙ የሚገኙ ስኬቶች ናቸው፡፡
በመልካም ፈቃዱ
Exit mobile version