አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ለአንድ ሀገር ዘላቂ ቀጣይነት መሠረት ከሚሆኑት ውስጥ ገለልተኛ ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ወቅቶች ሲቀያየሩና መንግሥታት ሲለዋወጡ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነቡ እንደ ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ያሉ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም፣ ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚተጉ ተቋማትን መገንባት አስፈላጊ ነው፡፡
ውግንናውን ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ያደረገው መከላከያ ሠራዊት ሰላም የመጀመሪያ ምርጫው እንደመሆኑ ሀገር ከመጠበቅ ባሻገር ከሕዝብ ጎን በመቆም በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ እገዛ ያደርጋል፡፡
ሀገርን ሊያጠቃ፣ ብሔራዊ ጥቅምን ሊነካ ለመጣ ጠላት ግን ዳር ድንበር ሊያስከብርና ሰላምን ሊያስጠብቅ፣ ሕይወትን እስከመገበር በሚደርስ ፅናት ከፊት ይሰለፋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከቀደሙት ጊዜያት ጀምሮ በተደራጀ አቅም፣ የሀገርን ዳር ድንበር ከማስጠበቅ ባሻገር ለቀጣናው ሰላም በማስከበር ሂደት ውስጥ ቀዳሚ ተሰላፊ ሆኖ እስከ ዛሬ ዘልቋል፡፡
ከኮሪያ ዘመቻ ጀምሮ በኮንጎ፣ በሱዳን አቢዬ፣ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል፡፡
በጀግንነት ብቻ ሳይሆን በጽናትና በሥነ ምግባር ባለው ታማኝነት የሚታወቀው መከላከያ ሠራዊት በእነዚህ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ውስጥ ባለው ተሳትፎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቅናን አግኝቷል፡፡
በእርግጥ ኢትዮጵያ ጀግንነት አዲስ ነገሯ አይደለም፤ ዓድዋና ካራማራ ላይ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ያደረገቻቸው ዘመቻዎች ስኬታማ የሆኑት በሠራዊቱና በሕዝቡ የጀግንነት ገድል ነው፡፡
ይህም ለሀገር መስዋዕት የመሆንና በጽናት የመቆም ባሕል እስከ ዛሬ ድረስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መለያ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
በዘመናዊው ዓለም ወታደራዊ ጥንካሬን በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ማሳደግ የሚጠይቅ በመሆኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዛሬ ላይ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በዘመናዊ የውጊያ ብቃትና ቴክኖሎጂዎች ራሱን አዘምኖ በዘመናዊ መሣሪያዎች በመታገዝ እየሰራ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመታገዝ የላቀ የሳይበር ደህንነትና የመገናኛ አውታሮች ዘመናዊ አቅሙን ገንብቷል፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የውስጥና የውጪ ፈተናዎች ሲፈራረቁባት እንደመቆየቷ ጠላት ደጇን ሳይረግጥ እንዲቆይ ካደረጉት ውስጥ ዋነኛው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ነው፡፡ በልበ ምሉዕነት ኢትዮጵያ ብርቱ ናት፤ ሉዓላዊነቷ አይደፈርም የምንለውም የማይደፈር ጠንካራ ሠራዊት ስላለን ነው፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጀግንነትን ከዘመናዊነት፣ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን ከዕውቀትና ስልጡን የሰው ኃይል ጋር አጣምሮ የያዘ በመሆኑ ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ ካለው ሚና ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰላምና ሰብዓዊ ተግባራት የኢትዮጵያን የጀግንነትና የመልካምነት ገፅታ እያሳየ ይገኛል፡፡
በቤተልሔም ግርማ

