አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል በተለያዩ ሁነቶች መከበር ጀምሯል፡፡
የብሩህ ተስፋ፣ የደስታና ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገሪያ ምልክት የሆነው ያሆዴ በሆሳዕና ከተማ ነው በድምቀት መከበር የጀመረው፡፡
በበዓሉ አከባበር ላይ ከሀዲያ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የተወጣጡ የቱሪዝም ዘርፍ አካላት የሀዲያን የባህል አልባሳትና ቅርሶች ለዕይታ አቅርበዋል፡፡
ለዕይታ ከቀረቡት መካከል በያሆዴ ሰሞን የሚዘወተሩ ባህላዊ ምግቦችን ጨምሮ ምግቦቹ የሚዘጋጁባቸውና የሚቀርቡባቸው ባህላዊ ቁሳቁሶችና ሌሎች ክዋኔዎች ይገኙበታል፡፡
ከባህላዊ ቅርሶቹ በተጨማሪ ለመድኃኒትነት ሲጠቀምባቸው የቆዩ የተለያዩ ዕጽዋትም በያሆዴ በዓል ዋዜማ ላይ ለዕይታ ቀርበዋል፡፡
የበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት በዛሬው ዕለት የጀመረ ሲሆን÷ የአተካና ባህላዊ ምሽት አንዱ የበዓሉ ድምቀት መገለጫ ነው፡፡
በጌታቸው ሙለታ

