Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ የአደባባይ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን – ወጣቶች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ መጪዎቹ የመስቀል ደመራ እና ኢሬቻ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ የበኩላችንን ኃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅተናል አሉ የከተማዋ ወጣቶች።

ሲሳይ ተማም የተባለ ወጣት ለፋና ዲጂታል እንደገለጸው÷ የአደባባይ በዓላት የኢትዮጵያን ባሕል፣ አንድነትና አብሮነት ለዓለም የሚያስተዋውቁ በመሆናቸው ወጣቱ ትልቅ ኃላፊነት አለበት።

 

ወጣቱ ጥላቻንና መከፋፈልን የሚያንጸባርቁ ሃሳቦችን በማስወገድ ሕብረ ብሔራዊነትንና አንድነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ አስገንዝቧል።

 

ከሀገር ውስጥና ከውጭ የሚመጡ እንግዶችን በክብር በመቀበልና በማስተናገድ የኢትዮጵያን መልካም እሴቶች ማሳየት እንደሚገባም ጠቁሟል።

 

ጉዱ ሸኩር የተባለ ወጣት በበኩሉ÷ የመስቀልና ኢሬቻ በዓላት በስኬት እንዲከበሩ የወጣቱ ድርሻ ከፍተኛ ነው፤ ለዚህም የከተማዋ ወጣቶች ለሰላም ዘብ ለመቆም ተዘጋጅተናል ብሏል፡፡

ወጣቱ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን በመተው ለሀገር ግንባታ እና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አመልክቷል።

 

የመስቀል ደመራና ኢሬቻ በዓላት በስኬት እንዲከበሩ ከአካባቢው የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የበኩሉን ለመወጣት መዘጋጀቱን ያነሳው ደግሞ ወጣት ፈይሳ ትቤሶ ነው።

 

ሰላም ለሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን የገለጸው ፈይሳ÷ ወጣቶች የሰላም አምባሳደሮች በመሆናቸው ከፋፋይ አካሄዶችን በመተው ለሀገር ልማት፣ አንድነትና ለበዓላቱ ስኬት በትብብር መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥቷል።

 

ወጣት እታለም ብርሃኑ ÷ በበዓላቱ ወቅት ሰላምን ለማደፍረስ የሚሞክሩ እንቅስቃሴዎችን ወጣቱ በጥንቃቄና በንቃት በመከታተል ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ብላለች።

 

በዓላቱ እሴታቸው ተጠብቆ በድምቀት እንዲከበሩ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ሃላፊነት እንዲወጣም ወጣቶቹ ጥሪ አቅርበዋል።

 

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version