Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመደመር መንግሥት እሳቤ የተቃኘው የልማት ጉዞ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ የሚገኙት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችና ተቋማት ለአንድ የምርጫ ዘመን ብቻ የሚያገለግሉ ሳይሆኑ ለትውልድ የሚሻገሩ ናቸው።
ይህ የትውልድ ቀጣይነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት ሕዝቡ በመንግሥትና በሥርዓቱ ላይ ያለውን እምነት ይበልጥ ሊያጠናክር ይችላል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ታሪካዊና መዋቅራዊ የሆኑ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሽግግሮችን እያደረገች ሲሆን÷ በዚህ ሽግግር ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።
ሀገሪቱ ካደጉትና ራሳቸውን ከቻሉት የአፍሪካ ቁንጮ ኢኮኖሚዎች ተርታ እንድትሰለፍ፣ የተጀመሩ የልማት ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠልና የዕድገት ሞተሮችን በስትራቴጂ መደገፍ ያስፈልጋል።
ይህ ሁለንተናዊ የልማት ጉዞ ከግብርና እስከ ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ ከከተማ ውበት እስከ ማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ ድረስ ሰፊ መስኮችን ያጠቃልላል። የልማት ጉዞውን በዘላቂነት ለማጠናከር ሰላምን ማስጠበቅ፣ የቴክኖሎጂና የምርምር ሥራዎችን ወደ ተግባር መለወጥ እንዲሁም መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት ቁልፍ ሚና አላቸው።
በተጨማሪም ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን ወደ ተግባር በመቀየር የምርት አቅምን ማሳደግ ይገባል። በጽናት ላይ የተመሠረተ የጋራ ትብብርም የልማት ግቦችን ከግብ ለማድረስ ታላቅ መሠረት ነው።
ዲጂታል ሽግግርን ማፋጠን የግብርና ምርታማነትን ከማረጋገጥና መሠረተ ልማትን ከማዘመን ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው። አንድ ዘመናዊ ኢኮኖሚ ያለ ጠንካራ የዲጂታል መሠረተ ልማት ሊራመድ አይችልም። የቴክኖሎጂ ሽግግርም በሁሉም ዘርፎች ቅልጥፍናን የሚጨምር አባዢ አቅም ነው።
ቢሮክራሲንና ሙስናን ለመቀነስ እንዲሁም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ኢንቨስተሮች ምቹ የንግድ ከባቢ ለመፍጠር የመንግሥት አሠራሮችን በቴክኖሎጂ ማገዝ ያስፈልጋል።
በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላምን በማስፈን፣ ተቋማዊ ግልጽነትን በመገንባትና ፈጠራን በመደገፍ የሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ዘላቂና ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ይቻላል።
በግብርናው ዘርፍ ሀገሪቱ ከግብርና መሪ ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር የምታደርገው ጥረት በስትራቴጂ እየተመራ ነው።
በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ለውጭና ለሀገር ውስጥ አምራቾች ምቹ ከባቢ በመፍጠር የጨርቃጨርቅ፣ የቆዳ፣ የፋርማሲዩቲካል እና የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ጀምረዋል።
ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን የኃይል፣ የፋይናንስና የግብዓት ችግሮች በመቅረፍ ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙና የሀገር ውስጥ ምርትን እንዲተኩ የሚያግዝ አገራዊ ንቅናቄ ነው።
በትምህርት ዘርፍ የትምህርትን ጥራት ለማሻሻል አዳዲስ የፈተና ሥርዓቶች፣ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና እና የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን በኦንላይን መስጠት ተጀምረዋል። የዘመናዊ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታም ትኩረት ተሰጥቶታል።
የኢትዮጵያ የልማት ጉዞ በሁሉም ዘርፍ ተስፋ ሰጪና ፈጣን ለውጦችን እያሳየ ይገኛል። ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ፣ የኑሮ ውድነትን መቆጣጠርና የመልካም አስተዳደር እሴቶችን ይበልጥ ማጠናከር የልማት ግቦቹ ሙሉ በሙሉ ከግብ እንዲደርሱ ወሳኝ መሠረቶች ናቸው።
በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ዕውን ለማድረግ የሁሉም ዜጎች፣ የግሉ ዘርፍና የመንግሥት የተቀናጀ ተሳትፎ መረጋገጥ ይኖርበታል።
በትዕግስት ግዛቸው
Exit mobile version