Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት ከመስከረም 19 እስከ 21 ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) 6ኛው ዙር የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት ከመስከረም 19 እስከ 21 በአዲስ አበባ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ይከበራል።

የቱሪዝም ሳምንቱን አስመልክቶ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ÷ በመደመር መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ በተወሰዱ የልማት እርምጃዎች ክልሉ ያሉትን የተፈጥሮ፣ የታሪክና የባህል ፀጋዎች ለመግለጥ ሰፊ ሥራዎች ተሰርተዋል።

የቱሪዝም ሳምንቱም እነዚህን ሀብቶች በስፋት ለማስተዋወቅና ከሀገር ውስጥና ከውጭ የሚመጡ ጎብኚዎችን ለመሳብ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘንድሮው የቱሪዝም ሳምንት ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከእስያና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚመጡ የቱሪዝም ባለሙያዎች፣ አስጎብኚ ማኅበራትና እንግዶች በመርሐ ግብሩ ይሳተፋሉ።

ይህም የኦሮሚያን እና የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብት ለዓለም አቀፍ ተሳታፊዎች ለማስተዋወቅ እና በዘርፉ አዳዲስ የትብብር እድሎችን ለመፍጠር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አብራርተዋል።

በቱሪዝም ሳምንቱ በሚዘጋጀው ኤግዚቢሽን ከተለያዩ ክልሎችና ከውጭ ሀገራት የሚመጡ ተሳታፊዎች የቱሪዝም ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን የፓናል ውይይት፣ የኦሮሚያ ቱሪዝም ሽልማት እና የሚስ ኦሮሚያ መርሐ ግብርም እንደሚካሄዱም አመልክተዋል።

በተጨማሪም በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ከቱሪዝም ጋር ለማስተሳሰር ከአስጎብኚ ማኅበራት ጋር ምክክርና ጉብኝት ይደረጋል ብለዋል።

ይህም በቀጣይ የኢሬቻ በዓልን ያማከሉ የቱሪዝም ፓኬጆችን ለማዘጋጀትና የበዓሉን ባህላዊ እሴት ለጎብኚዎች በተሻለ መልኩ ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

መርሐ ግብሩ የኦሮሚያንና በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን፣ ባህላዊ ትውፊቶችንና የቱሪዝም ምርቶችን በስፋት ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑ ገልጿል።

በግዛቸው ግርማዬ

Exit mobile version