አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ግብርና ከተለመደው የአመራረት ልማድ ወጥቶ ወደ ተደራሽና ሁለንተናዊ የምግብ ዋስትና ለመሸጋገር በሚያደርገው ጉዞ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።
በዘርፉ ከተመዘገቡ ስኬቶች ውስጥ በ2015 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ዋነኛ ተጠቃሽ ነው።
መርሐ ግብሩ ዛሬ የኢትዮጵያውያን ጓሮ የልማት ማዕከል በመሆን የዕለት ተዕለት የምግብ ፍላጎትን ከማሟላት በመሻገር ኢኮኖሚውንም የሚደግፍ ሆኗል።
በተጨማሪም የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን በማጠናከር የወጪ ንግድ አቅምን በማስፋትና ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የግብርና ዘርፉን በከፍተኛ ፍጥነት በመለወጥ ላይ ነው።
መርሐ ግብሩ የእንስሳት ዝርያን ማሻሻል፣ የዶሮና የዓሣ ጫጩቶች ማከፋፈል፣ የእንስሳት መኖ እና ዘመናዊ ቀፎዎችን ማቅረብ እንዲሁም የተሻሻሉ የእንስሳት ጤና አገልግሎቶችን ያካተተ ነው፡፡
በዚህም ዓመታዊ የወተት ምርት ወደ 13 ነጥብ 1 ቢሊየን ሊትር ከፍ ያለ ሲሆን፤ የእንቁላል ምርትን 9 ነጥብ 3 ቢሊየን እንዲሁም የዶሮ ስጋ ምርት 190 ሺህ ቶን ማድረስ ተችሏል፡፡
ይህም የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ከቤት ፍጆታ ባሻገር ገቢ ለማስገኘት እምቅ አቅም እንዳለው ማሳያ ነው።
የወጪ ንግድና የሀገር ውስጥ አቅርቦትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያግዘው የማር ምርት በተመሳሳይ ከፍተኛ እድገት የታየበት ሲሆን፤ በ2018 በጀት ዓመት ወደ 326 ሺህ ቶን አድጓል፡፡
የዓሣ ምርትን ለማሳደግ በተሰራው ሥራም በ2018 በጀት ዓመት 243 ነጥብ 8 ሺህ ቶን ማምረት ተችሏል።
በሌማት ትሩፋት ማዕቀፍ ውስጥ በአጠቃላይ 15 ሺህ 976 የወተት፣ 21 ሺህ 400 የዶሮ፣ 4 ሺህ የማር እና 2 ሺህ 433 የዓሣ ልማት መከወኛ መንደሮች ተቋቁመዋል።
እነዚህ ልዩ የልማት መንደሮች የዝርያ ማሻሻልን፣ የመኖ ስርዓቶችን፣ የእንስሳት ጤና አገልግሎቶችንና የወሳኝ ገበያ ትስስሮችን በይበልጥ እያጠናከሩ ይገኛሉ።
የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል ከማድረግ ባለፈ በግብርናው ዘርፍ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆን መሰረት እየጣለ ይገኛል።
በሶስና አለማየሁ

