Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የግብርና ምርታማነት እድገት በኢትዮጵያ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በቅርብ ዓመታት የኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ በዝናብ ላይ ብቻ የነበረውን ጥገኝነት በመቀነስና የሀገር ውስጥ የሰብል ምርትን በማሳደግ ከፍተኛ መዋቅራዊ ለውጦችን አድርጓል።
በመደመር መንግሥት የተዘረጉት ታላላቅ፣ መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ መሰረተ ልማቶች እንዲሁም የክላስተር እርሻ አሰራሮች ዋነኛ የለውጥ ስራዎች ናቸው።
በመስኖ ግብርና በተካሄዱ ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎች የተመዘገቡ ዋና ዋና ስኬቶች ለሺህ ዘመናት መሻሻል ርቆት የነበረውን ዘርፍ መለወጡን የሚያበስሩ ናቸው፡፡
ከዚህ ቀደም የሀገሪቱ ግብርና በዝናብ ላይ ብቻ የተመሰረተ በመሆኑ፤ በመስኖ የሚለማው መሬት ከጠቅላላው የታረሰ መሬት አንጻር እጅግ ዝቅተኛ ነበር፡፡ ይህም ምርታማነቱን አናሳ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የአዋሽ፣ የኦሞ፣ የዋቤ ሸበሌ እና ሌሎች የወንዝ ተፋሰሶችን በመጠቀም እንዲሁም በየአካባቢዎቹ አነስተኛ መስኖዎችን በማስፋፋት የሚለማው የመሬት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ118 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት የሚያስችሉ የመስኖ መሰረተ ልማት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
የስንዴ ምርትን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ፕሮግራምም በዘርፉ ከተከናወኑት ትልልቅ ስኬቶች አንዱ ነው።
ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎቷን በራሷ ለመሸፈን ከመቻሏም ባሻገር ምርቱን ወደ ውጪ መላክ ጀምራለች።
በኩታ ገጠም እርሻዎች በሄክታር የሚገኘውን የምርት መጠንም በምርጥ ዘር ስርጭት እንዲሁም በተስማሚ ማዳበሪያ አጠቃቀም ማሳደግ ተችሏል፡፡
ይህም የአነስተኛ አርሶ አደሮችን መሬት በኩታ ገጠም በማደራጀት ወጥ የሆነ የምርት ግብአት አጠቃቀምን፣ የተቀናጀ የመስኖ ፕሮግራም እንዲሁም ትራክተርና ኮምባይነር አጠቃቀምን ያጠቃልላል።
ቀደም ሲል ለእንስሳት እርባታ ብቻ ይውሉ በነበሩ ቆላማ አካባቢዎች በጸሐይ ብርሃን የሚሰሩ የውሃ መሳቢያዎች፣ የጠብታ መስኖ ስልቶች እና የወንዝ ማዞሪያ ግንባታዎች የውሃ አቅርቦትን አሳድገዋል።
በግብርና ማሽነሪዎችና ማዳበሪያዎች ላይ የተደረጉ የቀረጥ ነጻ መብቶች እና የገጠር ብድር አቅርቦት አርሶ አደሮችና ህብረት ስራ ማህበራት በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ አድርጓል።
በመስኖ እርሻ ከእህሎች በተጨማሪ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የቅባት እህሎች እና የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎች ምርትን በማሳደግ ከግብአት አቅርቦት እንዲሁም ከገበያ ትስስር ጋር የተያያዙ አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያሳዩት ዘርፉ የአየር ንብረት ለውጥን ወደሚቋቋም አሰራር እየተሸጋገረም ይገኛል።
በምህረት ደምሴ
Exit mobile version