አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2019 በጀት ዓመት በአማራ ክልል የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ እና የመሬት ይዞታ ምዝገባ በ66 አዳዲስ ከተሞች ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል አለ የክልሉ መሬት ቢሮ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ እብሬ ከበደ እንዳሉት፥ የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ እና የመሬት ይዞታ ምዝገባ በአዳዲስ ከተሞች ለማስጀመር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቅቋል።
ከዚህ ቀደም በ8 ሪ-ጂኦ ፖሊታን ከተሞችና በ6 ሌሎች ከተሞች በጥቅሉ 14 ከተሞች ላይ ብቻ የምዝገባ ሥራው ሲከወን መቆየቱን አስታውሰው፤ የከተማ መሬትን ከተለያዩ ሕገ ወጥነቶች ጠብቆ በመምራት ረገድም ጉድለቶች እንደነበሩ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የዘርፉን ችግር ለመቅረፍ የሚረዳ አሰራርን በመዘርጋት የተጀመረው የዲጂታል ሥርዓት ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ መሬትን መመዝገብ፣ አጠቃቀሙን መወሰን እና በአግባቡ ማስተዳደር ላይ እየተሰሩ ያሉ አበረታች ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
በልማት ተነሺዎች የሚታዩ ቅሬታዎችን በተመለከተም በቅድሚያ ካሳው በአግባቡ እንዲሰላ ማድረግ ላይ ትኩረት እንደሚሰጠው ገልጸው፤ በተገቢው መንገድ ተነሺዎቹ ጋር መድረሱን ማረጋገጥ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በኤልያስ አንሙት

