Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ሁለገብ የዲፕሎማሲ ስኬቶች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በመደመር ፍልስፍና ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ የውጭ ግኑኝነት ፖሊሲ በዓለም አቀፍ እና በቀጣናዊ መድረኮች ለተመዘገቡ ሁለገብ የዲፕሎማሲ ስኬቶች መሰረት የጣለ ነው።
ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷና በብሔራዊ ጥቅሟ ላይ የተመሰረተ ተለዋዋጭና ንቁ የዲፕሎማሲ አቅጣጫን በመከተል፣ ባለፉት ዓመታት ያጋጠሟትን ልዩ ልዩ ፈተናዎች በመሻገር አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መክፈት ችላለች፡፡
ይህ ስኬት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖራትን የንግድ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተደራሽነት ይበልጥ ያሰፋው ሲሆን፣ ድምጿም በዓለም አቀፍ መድረኮች በግንባር ቀደምትነት እንዲሰማ አስችሏል።
ከዋና ዋናዎቹ ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ፍሬዎች መካከል ኢትዮጵያ የብሪክስ ስብስብ ሙሉ አባል መሆኗ እና በጉባኤዎቹ ላይ ያሳየችው የጎላ ተሳትፎ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡
በዚህ ዓለም አቀፋዊ መድረክ አማካኝነት ኢትዮጵያ ከአባል ሀገራት ጋር ያላትን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነት ያጠናከረች ሲሆን፤ ለዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የምታደርገው ጥረትም ሙሉ ድጋፍ እንዲያገኝ አድርጋለች።
ከህንድ እና ከሩሲያ ጋር በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በኢንቨስትመንትና በታዳሽ ኃይል ልማት መስኮች የተደረጉት ስምምነቶች የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያፋጥኑ ስትራቴጂካዊ ርምጃዎች ናቸው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመዘገቡት ስኬቶች ባሻገር፣ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ደግሞ ኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት፣ የኃይል ማስተላለፊያ እና የድንበር ተሻጋሪ ንግድ ማቀላጠፊያ ፕሮጀክቶችን በመዘርጋት የቀጣናዊ ትስስር ግንባር ቀደም መሪ መሆኗን አረጋግጣለች።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና የፓን አፍሪካኒዝም ማዕከል በመሆኗም፤ እንደ ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጉባኤ፣ የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ እና የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤዎችን ለማስተናገድ መመረጧ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት የሚያሳይ ነው።
ሀገራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በማጠናከር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከ131 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ ሀገር መመለስ ተችሏል፡፡
እንዲሁም ከ160 በላይ በሚሆኑ የኢንቨስትመንት መድረኮች ላይ በመሳተፍ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብና አዳዲስ የንግድ ትስስሮችን በመፍጠር የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ስኬታማ እንዲሆን ተደርጓል።
በአብረሃም አበራ
Exit mobile version