Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዘመኑን የዋጀው የኢትዮጵያ አየር ኃይል፡ የሰማዩ ንስር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰማይ የሀገር የመጨረሻ ድንበር ነው፤ በዚያ ድንበር ላይ የሉዓላዊነት ጥበቃ ይጀምራል።

የሀገርን የአየር ክልል በጥንቃቄ በንስር ዐይን መቃኘት፣ ማንኛውንም ስጋት በፍጥነት መለየትና በብቃት መመከት የአየር ኃይል ተቀዳሚ ተልዕኮ ነው።

ይህን ተልዕኮ በጀግንነትና በመስዋዕትነት ለዘመናት የተወጣው የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ ዛሬ የትናንትን የውጊያ ተሞክሮ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂና ከተቋማዊ ሪፎርም ጋር በማጣመር የሰማዩን ድንበር ለመጠበቅ ዝግጁ ሆኖ ቆሟል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90 ዓመታትን በላቀ የውጊያ ተሞክሮ፣ በጀግንነትና በመስዋዕትነት ተሻግሯል። በዚህ ረጅም ጉዞም የኢትዮጵያን የአየር ክልል በጀግንነት በመጠበቅ፣ ሀገርን በማጽናትና በተለያዩ የውጊያ ሁኔታዎች የተልዕኮ አፈጻጸም ተሞክሮን በማከማቸት የራሱን ልዩ ታሪክ ጽፏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደሚሉት÷ አየር ኃይሉ ኢትዮጵያን ለመድፈር ለሞከሩ ኃይሎች ሁነኛ መድሃኒት ሆኖ ሀገር ያጸና ተቋም ነው፡፡

የዚህ ታሪክ ዋነኛ መገለጫ ጀግንነት ብቻ ሳይሆን ተልዕኮን በብቃት የመፈጸም ባህል ነው። የውጊያ ሁኔታዎችን በትክክል መገምገም፣ ተገቢውን የአየር ኃይል መጠቀምና ተልዕኮን በተቻለ መጠን በትንሽ ኪሳራ በድል ማጠናቀቅ የአየር ሃይሉ መገለጫዎች ናቸው፡፡ የትናንት የውጊያ ልምዱም ዛሬ ለሚገነባው ዘመናዊ አቅም መሠረት እንዲሆን አስችሏል።

ዛሬ ይህ ታሪክ በአዲስ የቴክኖሎጂ ቋንቋ እየተተረጎመ ነው። የድሮን ቴክኖሎጂ፣ ዘመናዊ የውጊያ አውሮፕላኖች፣ የአየር ክትትልና የመረጃ ሥርዓቶች እንዲሁም የሳይበር አቅም የዘመኑ የአየር ኃይል አቅም አካላት ሆነዋል።

በተቋማዊ ሪፎርም የተቃኘው የአየር ኃይሉ ለውጥም ከመሣሪያ ማዘመን ባሻገር የሰው ኃይልን፣ የምርምርና ልማትን፣ የጥገናና ማምረት አቅምን በማጠናከር ላይ አተኩሯል፡፡ በተለይ ከውጭ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ከመሆን ባሻገር በራስ አቅም ማምረትና መጠገን መቻል የዘመኑ የአየር ኃይል ግንባታ ወሳኝ አቅጣጫ ሆኗል።

የሰው አልባ አውሮፕላን ማምረት የዚህ ለውጥ አንዱ ማሳያ ነው። በ2017 ዓ.ም የተመረቀው ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ ለሲቪልና ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለማምረት የተቋቋመ ሲሆን ÷ ይህም በመከላከያ ዘርፍ የቴክኖሎጂ ራስን መቻል ጥረት አካል ነው፡፡

የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳም ተቋሙ ለ90 ዓመታት “የሰማይ ጋሻ” ሆኖ ሉዓላዊነትን ሲጠብቅ መቆየቱን ያወሳሉ፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ÷ አየር ኃይሉ የብሔራዊ ኩራት፣ የቴክኖሎጂ እድገትና የተልዕኮ ጽናት ምልክት ሆኖ በአየር ዘርፍ የላቀ ብቃትን ለማስቀጠል ቁርጠኛ ነው።

ይህ ዝግጁነት የሚመዘነው በሚበሩ አውሮፕላኖች ብዛት ብቻ አይደለም። በአብራሪዎች ብቃት፣ በመሐንዲሶችና በቴክኒሻኖች እውቀት፣ በመረጃ ሥርዓት፣ በጥገና አቅም፣ በፍጥነት ውሳኔ የመውሰድ አቅምና በተልዕኮ ጊዜ የሚፈለገውን ምላሽ በትክክል መስጠት በሚችል የተቀናጀ አቅም ነው።

በዚህ ረገድ የወደፊቱ የአየር ኃይል ከዛሬው የበለጠ የቴክኖሎጂ ብቃትን ይጠይቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በ90ኛ ዓመት በዓሉ ላይ አየር ኃይሉ ያዳበረውን የአራተኛ ትውልድ የውጊያ አቅም በ2030 ወደ አምስተኛ ትውልድ ለማሸጋገር መታቀዱን ገልጸዋል።

በዚህ ሁሉ ውስጥ የአየር ኃይሉ የትናንት ጀግንነት እና የዛሬ ዝግጁነት ተለያይተው የሚታዩ ጉዳዮች አይደሉም። ትናንት በጀግንነት የተጠበቀው ሰማይ ዛሬ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በሰለጠነ ሰው ኃይልና በተቋማዊ ብቃት እየተጠበቀ ነው።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ የትናንት የውጊያ ድሎችን ብቻ የሚዘክር ታሪክ አይደለም፤ ከትናንት ተሞክሮ ተምሮ ለነገ የሚዘጋጅ ተቋም የመገንባት ጉዞም ነው።

በውጊያ የተፈተነ ጀግንነት፣ በትንሽ ኪሳራ ተልዕኮን በድል የማጠናቀቅ ተሞክሮ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ አቅምና ሁለንተናዊ ዝግጁነት ተደምረው የሰማዩን ንስር የነገውን ሰማይ እንዲቃኝ እያዘጋጁት ነው።

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version