Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሥነ-ምህዳርን በመጠበቅ ረገድ አበርክቶው የጎላ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እያከናወነች የምትገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከችግኝ ተከላ ባለፈ ሥነ-ምህዳርን በመጠበቅ ረገድ አበርክቶው የጎላ ነው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ።

በፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የተመራ ከፍተኛ ልዑክ ቡድን በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው 81ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

ፕሬዚዳንት ታዬ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳትን ለመቀነስ የሚያስችል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።

መርሃ ግብሩ ሥነ-ምህዳርን በመጠበቅ ረገድ አበርክቶው የጎላ ነው ብለው እስካሁን ድረስም ኢትዮጵያ ከ56 ቢሊየን በላይ ችግኞችን መትከል መቻሏን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ታዬ ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ከሚገኘው የዲጂታል ሥርዓትም ተጠቃሚ ለመሆን በዘርፉ በርካታ ተግባራት እያከናወነች እንደምትገኝ አንስተዋል።

በዘርፉ በእውቀትና በክህሎት የሰለጠነ በቂ የሰው ኃይል ለማፍራት ሰፊ ሥራዎች መሰራታቸውንና በዚህ ረገድም የ5 ሚሊየን ኮደሮች ስልጠና ፕሮግራምን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ልማትን በትኩረት እየሰራችበት እንደሆነና በቅርቡ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ሥራ እንደሚጀምር ጠቁመዋል።

በቴዎድሮስ ሳህለ

Exit mobile version