Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሎጆች – የኢኮኖሚው ሞተሮች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ በአዲስ ምዕራፍ ውስጥ ይገኛል። መንግሥት ቱሪዝምን ለማነቃቃትና ለሀገር ኢኮኖሚ የሚጫወተውን ሚና ለማሳደግ የወሰዳቸው ቁርጠኛ እርምጃዎች የሚጨበጥ ውጤት እያስገኙ ነው።

ነባር መዳረሻዎችን ከማደስና ከማዘመን ባለፈ፣ አዳዲስ የተፈጥሮና የባህል ሀብቶችን ማልማት ተችሏል። በተለይም በየመዳረሻዎቹ የተገነቡት ዘመናዊና ውብ ሎጆች የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ በመጨመር ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ።

በመደመር እሳቤ፣ ኢትዮጵያ በርካታ የተፈጥሮ፣ የታሪክ እና የባህል ሀብቶች ባለቤት ብትሆንም፣ እነዚህ ሀብቶች ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሳይቀየሩ ለዘመናት ቆይተዋል። የሎጆች ግንባታ እነዚህን ድብቅ ሀብቶች ወደ ተጨባጭ ሀብት የመቀየሪያ መሣሪያዎች ሆነው እያገለገሉ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታኅሣሥ 01 ቀን 2016 ዓ.ም. በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኘውን የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ “ቀደም ሲል ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ታሪካዊ ቦታዎችን ተመልክተው በፍጥነት ይወጡ ነበር፤ አሁን ዘመናዊና ማረፊያ የሚሆኑ ሎጆች መገንባታቸው ጎብኚዎች ለአያሌ ቀናት እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል” ብለዋል።

በዚህም መንግሥት ባለፉት ዓመታት በገበታ ለትውልድና ገበታ ለሀገር የገነባቸው የሀላላ ኬላ ሪዞርት፣ የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ፣ የሀሮ ደንዲ ሎጅ፣ የቤኑና ሎጅ፣ የኒዒን ሌ ፓልም ስፕሪንግ ሎጅ፣ የወንጪ ኢኮ ሎጅ፣ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት፣ የዲንሾ ሎጅ፣ የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት፣ የሪራ ኢኮ ሎጅ እና የሶፍ ዑመር ሎጅ ለቱሪዝሙ ዕድገት ትልቅ የመወጣጫ መሰላል ሆነዋል።

እነዚህ ሎጆች ለኢትዮጵያ ማክሮ-ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ እያመጡ ያሉ አዳዲስ የኢኮኖሚ ሞተሮች ሲሆኑ እያመጡ ያሉትን ውጤት ማየት አስፈላጊ ነው።

ቱሪዝም ከአምስቱ የሀገራችን የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ተደርጎ በመሰራቱ የውጭ ምንዛሬን በማሳደግ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ ኢኮኖሚውን በማነቃቃትና የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በማሳደግ ረገድ አመርቂ ውጤት እያመጣ ይገኛል።

የዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ ሲሆን በ2018 ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ጎብኝተው ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። ይህም በሀገሪቱ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ያግዛል።

የሎጆቹ መገንባት በአካባቢው ለሚገኙ ወጣቶችና የማህበረሰብ ክፍሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ይህም በሆቴልና መስተንግዶ፣ በቱሪስት አስጎብኚነት፣ በባህል ዕቃዎች ሽያጭ እና በትራንስፖርት ዘርፍ የዜጎችን ገቢ እያሻሻለ ይገኛል።

የአካባቢ ኢኮኖሚን ከማነቃቃትና መሠረተ ልማትን ከማስፋፋት አንጻር ፕሮጀክቶቹ በተገነቡባቸው አካባቢዎች የመንገዶች፣ የንጹሕ መጠጥ ውሃ፣ የኤሌክትሪክ እና የኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማቶች ተደራሽ ስለሚሆኑ የአካባቢውን ማህበረሰብ የኑሮ ደረጃ እየቀየሩት ነው። ሎጆቹ ከአካባቢው ማህበረሰብ ግብዓቶችን በመግዛት የገበያ ትስስር እያፈጠሩ ነው።

መንግስት የግል ባለሀብቶች በቱሪዝም ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ በፖሊሲ የተደገፉ የማበረታቻ እና አስቻይ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል። ብዙዎቹ የለሙት ሎጆችና ሪዞርቶችም ባለሀብቶች ከመንግስት ጋር በአጋርነት ያከናወኗቸው ናቸው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት በሰጠው ትኩረት የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ከፍተኛ እድገት እያሳየ ሲሆን በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የገንዘብ ፍሰት እንዲጨምር አድርጓል። በ2018 ብቻ ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እነዚህን አዳዲስ ሎጆች፣ ፓርኮች እና ሁነቶች እንዲጎበኙ በማድረግ ከ79 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል።

በአጠቃላይ እነዚህ የገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ያላትን ተፈጥሯዊና ባህላዊ ሀብቶች ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ አቅም በመቀየር፣ ሀገሪቱ በረጅም ጊዜ የምታስመዘግበውን ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት በከፍተኛ ሁኔታ እየደገፉ ይገኛሉ።

በታሪኩ ለገሰ

Exit mobile version