Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከጎስቋላ ገጽታ የዜጎችን ክብር ወደ ጠበቀ ውብ መኖሪያ የተቀየረው ቅጠል ተራ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ቅጠል ተራ የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክት አካባቢውን ከተበላሸ ገጽታ የዜጎችን ክብር ወደ ጠበቀ ውብ የመኖሪያ ቤትና ስፍራ ቀይሯል አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባዋ ትላንት አመሻሽ ላይ ተመርቆ ለነዋሪዎች የተላለፈውን የቅጠል ተራ የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክት አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
“ሁሉም ቀና ቢያስብ፣ ሰው ለሰው ቢፋቀር፣ ሁሉም ቢተባበር የት እንደርስ ነበር!” ሲሉ መልዕክታቸውን የጀመሩት ከንቲባ አዳነች ለዓመታት ነዋሪዎቻችን የጎርፍ እና የእሳት አደጋ ተጋላጭ የነበሩበት ታሪክ ተቀይሯል ብለዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ከነበረው የተበላሸ ገፅታ ዛሬ የዜጎቻችንን ክብር ወደ ጠበቀ ውብ የመኖሪያ ቤትና ስፍራ ተሸጋግረው በደስታ ሲኖሩ ማየት ወደር የሌለው ደስታ ይሰጣል ነው ያሉት።
“ዋናው ጥያቄ በሀገራችን ዋና ከተማ ውስጥ እንዴት ብዙ ዜጎቻችን እንደዛ አይነት አስቸጋሪ አኗኗር ውስጥ ለዓመታት ኖሩ፤ ዛሬስ ሁሉም በዚህ ፍጥነት እየተለወጠ ያለው እንዴት ነው?” የሚለው ነው ሲሉም አንስተዋል፡፡
ይህን ስራ እውን ያደረግነው ብዙ አካላትን በማስተባበርና በመደመር ነው፤ ከያለበት ያለውን እውቀት፣ ሀብትና ጉልበት ሳንሰስት ደምረናል ብለዋል፡፡
ሁሉም በየአቅሙ በፋይናንስ፣ በእውቀት፣ በጉልበት፣ በዲዛይን እና በግንባታ ሥራው ላይ በንቃት በበጎ ፍቃድ መሳተፉን ጠቁመው÷ ነዋሪዎችም ለተሻለ ልማት የለውጥን ተስፋ ሰንቀው ትልቅ ትብብር አድርገዋል ብለዋል፡፡
ይህ ሁሉ ጥረት አንድ ላይ ተደምሮ ትልቅ አቅም በመሆን ይህን የመሰለ የመኖሪያ መንደር እና አካባቢን ፈጥሯል፤ ቅጠል ተራም ታሪኩ መቀየሩን አመልክተዋል፡፡
“አንድ ላይ ተደምረን ለጋራ ራእይ እየተባበርን፣ በቅንነት፣ በትጋት እና እውነተኛ አገልጋይነት አብረን ስንሰራ ብዙ ሀብቶቻችን ተደምረው የሁላችንንም የጋራ ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጡ፣ የዜግነትን ክብር የሚያልቁ፣ አዳዲስ እድል እና ሀብት እንደሚፈጥሩ አይተናል” ነው ያሉት ከንቲባዋ።
ስለዚህ በማንኛውም ነገር በጋራ እንቁም፤ ትብብራችንንም ይበልጥ እናጠናክር፤ ለበለጠ ሀገራዊ ስኬት በመተማመን አብረን እንትጋ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
Exit mobile version