አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አካታች እና ፍትሃዊ የሆነ ዓለም አቀፍ ሥርዓት አስፈላጊ ነው አሉ የቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን።
በ81ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ቱርክ ለባለ ብዙ ወገን ተቋማት ድጋፍ እንዳላትና የበለጠ አካታች እና ፍትሃዊ የሆነ ዓለም አቀፍ ሥርዓት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በዚህም አፍሪካ፣ እስያ፣ ላቲን አሜሪካ፣ አውሮፓ እና ሌሎች ሁሉም ቀጣናዎች በራሳቸው ተሞክሮ እና ፍላጎት በዓለም አቀፉ ሥርዓት ውስጥ ፍትሐዊ ውክልና ሊኖራቸው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ፕሬዚዳንቱ ነባሩ የተባበሩት መንግስታት መዋቅር የ190 በላይ ሀገራትን ፍላጎት በአምስት ቋሚ አባል ሃገራት ድምጽ ማስጠበቅ እንደማይችልና ሁሉንም አባል ሃገራት ያቀፈ የበለጠ የተጠናከረና ውጤታማ የጠቅላላ ጉባኤ ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የተመረጡ አባላት ለተወሰነ የሥራ ዘመን የሚያገለግሉበት እና እንደገና ለመመረጥ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እምነት ማግኘትን የሚጠይቅ ሥርዓት በመቅረጽ፣ የበለጠ ጠንካራ እና ውጤታማ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።
ዓለም በአሁኑ ወቅት የሚያስፈልጋት የመለያየት ግንብ ሳይሆን አዳዲስ ድልድዮች ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ አካታችና ትብብርን የሚያጠናክር ሥርዓት አስፈላጊ ነው ማለታቸውን አናዶሉ ዘግቧል።
በቴዎድሮስ ሳህለ

