አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ ቀንድ የምጣኔ ሃብት ውህደት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የከፈተ ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መንግሥታት ትብብር ይፋ ተደርጓል።
ይህ ታላቅ ፕሮጀክት በጅቡቲ የሚገኘውን የዳመርጆግ ኢንዱስትሪ ፓርክ በኢትዮጵያ ከሚገኘው ደወሌ ጋር የሚያገናኝ ድንበር ተሻጋሪ የተጣራ የነዳጅ ምርቶች ማጓጓዣ ቧንቧ ዝርጋታ ነው።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በምዕራብ አፍሪካው ግዙፍ የኢንዱስትሪ ተቋም ዳንጎቴ ግሩፕ መካከል በተደረገ የጋራ አጋርነት የሚከናወነው ፕሮጀክቱ÷ ለአፍሪካ ሀገራት የውስጥ ካፒታል አጠቃቀምና ዘላቂ የመሠረተ ልማት አርአያ የሚሆን ነው።
የዚህ ልማት ዋና አካል በሁለቱም ጫፎች የተገነቡ የማከማቻ ዲፖዎች ያሉት የ120 ኪሎ ሜትር የነዳጅ ማጓጓዣ ቧንቧ መስመር ነው።
ላለፉት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያና ጅቡቲ የንግድ መስመር በኩል የሚደረገው አብዛኛው የነዳጅ እንቅስቃሴ በከባድ የነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች ላይ የተመሠረተ ነበር።
የነዳጅ ማጓጓዣ ሥርዓቱ ወደ ቧንቧ መስመር መሸጋገሩ ለረጅም ጊዜ መሰናክል ሆነው የቆዩ በርካታ ፈተናዎችን መቅረፍ ያስችላል፡፡
መስመሩ በአውራ ጎዳናዎች የሚታየውን የከባድ ተሽከርካሪዎች ጭንቅንቅ እና የድንበር ማለፊያ እንቅፋቶችን በማስወገድ የጭነት ወጪንና የማጓጓዣ ጊዜን በእጅጉ ይቀንሳል።
በዳመርጆግና በደወሌ የሚገኙት የነዳጅ ማከማቻ ዲፖዎች የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂካዊ የነዳጅ ክምችት ያጠናክራሉ፤ ይህም የሀገር ውስጥ የነዳጅ ሥርጭትን ከገበያ መዛባትና ከአቅርቦት መቋረጥ ይከላከላል።
በዓመት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የረጅም ርቀት የቦቴ ጉዞዎችን በቧንቧ መስመር መተካቱ የካርበን ልቀትን ከመቀነስ ባለፈ የአውራ ጎዳናዎችን መጎዳት ያቃልላል እንዲሁም በማጓጓዝ ወቅት የሚከሰት የነዳጅ ብክነትን ያስቀራል።
ፕሮጀክቱ ለዋና ዋና የአፍሪካ መሠረተ ልማቶች ሀገራት ለጋራ እድገታቸው መደጋገፍ እና መተባበር እንደሚገባቸው ያሳያል።
በሁለቱ ሀገራት መንግሥታት መካከል የተገነባው ይህ አጋርነት የሀገር ሉዓላዊ ሃብትን ከግል ባለሃብቶች የካበተ ልምድ ጋር ያጣመረ ግዙፍ መሰረተ ልማት ነው።
የፕሮጀክቱ ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅሞች ከድንበር ተሻጋሪ የነዳጅ ማጓጓዝ በላይ በግንባታም ሆነ በሥራ ማስጀመሪያ ወቅት ፕሮጀክቱ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤የልምድና ክህሎት ሽግግርን ያሳልጣል፡፡
የአፍሪካ ካፒታልና ቀጣናዊ አጋርነቶች ውስብስብ የመሠረተ ልማት ፍላጎቶችን በቀጥታ መፍታት እንደሚችሉ ያረጋገጠም ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳመላከቱት÷ የነዳጅ ቧንቧ መስመሩ ከነዳጅ ማጓጓዣነት በላይ ለተሳሰረና ለጽኑ የአፍሪካ ምጣኔ ሃብት ራዕይ መሳካት እንዲሁም የጋራ ብልጽግና ላይ የተደረገ ንቁ ኢንቨስትመንትና የአህጉራዊ ትብብር አዲስ መለኪያ ነው።
በምህረት ደምሴ

