Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ስለ ሰው ልጅ ክብር ያደረገችው ሙግት በሚያ ሞተሊ አንደበት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞተሊ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ጉባዔን ጨምሮ በዓለም መድረክ ስለ ሰው ልጅ ክብር እና እኩልነት ስትሞግት መቆየቷን ምስክርነት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ስለ ሰው ልጅ ክብር፣ እኩልነት እና ነጻነት በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያደረገችው የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ሙግት በታሪክ የተሰነደ ደማቅ ዐሻራ ነው።

በተለይም የጥቁር ሕዝቦችን ክብር ለማስጠበቅ እና የቅኝ ግዛትን ሥርዓት ለመታገል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያደረገቻቸው ጥረቶች በዓለም የፍትሃዊነት እና እኩልነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ አላቸው።

ኢትዮጵያ በሊግ ኦፍ ኔሽንስ፣ በተባበሩት መንግሥታት፣ በጸረ-አፓርታይድ ትግል መድረኮች እና በአፍሪካ ህብረት ስለ ሰው ልጅ እኩልነት እና ክብር፣ ስለ ሀገራት ሉዓላዊነት እና ስለ ቅኝ ግዛት ኢፍትሃዊነት ሞግታለች፣ ታግላለች፣ አታግላለችም።

ዘረኝነትን በመቃወም እና ፍትሃዊነትን በማስፈን ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የካሪቢያን ጥቁሮች ተወካይ ሆነው የቀረቡት የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞተሊ በተባበሩት መንግሥታት 81ኛ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ ለጥቁር ሕዝቦች የዋለችውን ውለታ አውስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ በጉባዔው ባደረጉት ንግግር÷ ዓለም አቀፍ ተቋማት አግላይነትን በማስወገድ ለሰው ልጆች ክብር እና እኩልነት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለውጦችን ማስተዳደር ከፈለግን፣ በዋናነት እያንዳንዱን የሰው ልጅ እኩል ዋጋ እንዳለው እና ክብር እንደሚገባው ልናስብ ይገባል ነው ያሉት።

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በፈረንጆቹ ጥቅምት 4 ቀን 1963 “አንዱን ዘር የበላይ፣ ሌላውን ደግሞ የበታች አድርጎ የሚፈርጀው ፍልስፍና ሙሉ በሙሉ ተወግዶ እስካልተጣለ ድረስ ዘላቂ ሰላም ሊኖር አይችልም” የሚለውን ንግግራቸውን በድጋሚ አስተጋብተዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞተሊ።

ንጉሱ በወቅቱ ያደረጉት ንግግር ከአሁኑ ዘመን የዓለም ቀውሶች፣ የዘር መድልዎ፣ የጦርነት ማቆም እና የሰላም ጥሪዎች እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት መዋቅራዊ ለውጥ አስፈላጊነት ጋር የሚገናኝ መሆኑን አስረድተዋል።

የሰው ልጅ ሁሉ እኩል ዋጋ አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሯ÷ በአፍሪካውያን እና ካሪቢያን ሕዝቦች ላይ ለደረሰው የቅኝ ግዛት ታሪካዊ በደል የካሳ ክፍያ እንዲፈጸም በድጋሚ ጠይቀዋል።

ሚያ ሞተሊ በአንደበታቸው እንደመሰከሩት ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስራች ሀገር ከመሆኗም በላይ ስለ ጥቁር ሕዝቦች፣ ስለ ፍትሐዊነት እና ስለ ዓለም ሰላም እና መረጋጋት በዓለም አቀፍ መድረኮች ስትከራከር ቆይታለች።

የአፍሪካውያን የነጻነት ቀንዲል የሆነችው ኢትዮጵያ የአፍሪካውያንን ሰብዓዊ ክብር ለማስመለስ ትልቅ ሚና ስትጫወት ቆይታለች።

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version