አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለቀጠናዊ ትስስርና የጋራ እድገት በቁርጠኝነት ትሰራለች አሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ፡፡
የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የፋይናንስ ሚኒስትሮች ስብሰባ በኬንያ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ሚኒስትሩ በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ቀጣናውን በመሰረተ ልማት የሚያስተሳስሩ ፕሮጀክቶችን እየገነባች እንደምትገኝ አንስተዋል፡፡
ለአብነትም በቅርቡ የተጀመረው የኢትዮ-ጅቡቲ የነዳጅ ማስተላለፊያ ፕሮጀክት የቀጣናውን የኢነርጂ ደህንነት እንደሚያጠናክርና የሎጂስቲክስ ወጪዎችን እንደሚቀንስ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ማስተላለፊያ ኔትዎርክ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበር መሆኗን ጠቅሰው፤ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ አማካኝነት በቀጣናው ንፁህ የኃይል አቅርቦት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተች መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ በተካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የንግድ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎችን እንደምትደግፍ ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ለኃይል ዘርፍ ውህደት ቁልፍ የሆኑ ችግሮች የተለዩበትን የቀጣናዊ የኃይል ጥናትና ክትትል ውጤት እንደምትቀበል የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የተቋቋመውን የንግድ አመቻች ኮሚቴ እንደምታበረታታም አመልክተዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች ተፅዕኖ ውስጥ እየገባ መሆኑን በመጠቅስ፣ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን ማጠናከር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ልማት አጋር የሆነው የአረብ ባንክ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር የፈጠረውን አጋርነት አድንቀው፤ ባንኩ በኢትዮጵያ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ውስጥ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ በቀጣናው ንግድን ማጠናክር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን እንዲሁም በአባል ሀገራት መካከል ቀጣይነት ያለው ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ስምምነት ላይ መደረሱን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
በሚኪያስ አየለ

