Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢሬቻ፡ የፍቅር፣ የምስጋናና የአንድነት ውብ ህብረ-ቀለም

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በበርካታ ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ቋንቋዎችና ባህላዊ ህብረ-ቀለማት የደመቀች፤ ማህበራዊ ገመዷን አጥብቀው የሚያስተሳስሩ ድንቅ ሰብዓዊና መንፈሳዊ እሴቶች የታደለች ሀገር ነች።
ከእነዚህም መካከል በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ከጥንት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ፤ ለረጅም ዘመናት በድምቀት ሲከበር የኖረው የኢሬቻ በዓል በዋነኛነት ይጠቀሳል።
የክረምቱ ጨለማና የጭጋግ ወቅት አልፎ በብርሃንና በአበባ የደመቀው መስከረም ወር ሲጠባ የሚከበረው ይህ በዓል፤ ታላቅ የምስጋና፣ የፍቅርና የጽኑ አብሮነት መገለጫ ነው።
ኢሬቻ ፈጣሪ ላደረገው መልካም ነገር ሁሉ ምስጋና የሚቀርብበትና ለሚቀጥለው ዘመን ደግሞ ሰላም፣ ፍቅርና በረከት የሚለመንበት ዘርፈ ብዙ እሴቶችን ያቀፈ በዓል ነው።
ሕዝቡ የህይወትና የልምላሜ ምልክት የሆነውን አረንጓዴ ሳር እና አበቦችን በእጁ ይዞ ወደ ወንዝ ወይም ሐይቅ በመሄድ፤ ፈጣሪ ክረምቱን በሰላም አሳልፎ ለብርሃናማው ወቅት ስላደረሰው በታላቅ ትህትናና ፍቅር ያመሰግናል።
ይህም የሰው ልጅ ከተፈጥሮና ከፈጣሪው ጋር ያለውን ዘላቂ ቁርኝት የሚያጸባርቅ ህያው መስታወት ነው።
የኢሬቻ በዓልን ልዩ የሚያደርገውና ድምቀቱን የሚያጎላው ሁነት ደግሞ ያለ ምንም የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የጎሳ ልዩነት ሰዎችን በአንድ ጥላ ስር የማስተሳሰር እሴቱ ነው።
በዓሉ ሲከበር እርስ በእርስ መቀራረብ፣ ይቅር መባባልና የወንድማማችነት መንፈስ ይነግሳል።
ከኦሮሞ ሕዝብ ባሻገር የኢሬቻ በዓል የሌሎች በርካታ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችም ተሳትፎ የሚያደርጉበትና ወንድማማችነታቸውን የሚያጎሉበት የጋራ መድረክ ነው።
የየራሳቸውን ባህላዊ አልባሳት ለብሰው፣ በፍቅርና በመከባበር ከኦሮሞ ወንድሞቻቸው ጋር ተቀላቅለው ሲያከብሩ ማየት የኢትዮጵያን ህብረ-ቀለማዊ ውበት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
እርስ በእርስ መከባበር፣ መተሳሰብና መደጋገፍ በግልጽ የሚንጸባረቅበት ይህ በዓል የሀገራዊ አንድነት ማሰሪያ ውል ሆኖ ያገለግላል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓለም አቀፍና በሀገር አቀፍ ደረጃ እየደመቀና የብዙዎችን ቀልብ እየሳበ የመጣው የኢሬቻ በዓል በመጪው መስከረም 23 እና 24 ቀን በታላቅ ድምቀት ይከበራል።
ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ለዓለም ያበረከተው ታላቅ ስጦታ እንደመሆኑ መጠን፤ በዓሉ የሚያስተላልፈውን የሰላም፣ የእርቅና የጸና የአብሮነት መልዕክት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል፡፡
በመልካም ፈቃዱ
Exit mobile version