Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽል ዘላቂ መሠረት ተጥሏል – በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽሉ ዘላቂ መሠረቶች እየተጣሉ ይገኛሉ አሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)።

የኢትዮጵያ የሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ የ50 ዓመታት ጉዞንና የቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚዳስስ ሀገር አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እንዳሉት ፥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽሉና ሀገራዊ የዲጂታል ሽግግርን የሚያፋጥኑ ዓበይት እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡

በዚህም የሀገሪቱ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ17 ሚሊየን ወደ 65 ሚሊየን ማደጉን በማንሳት የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት መዘርጋቱ፣ ከ50 ሚሊየን በላይ ዜጎች የተመዘገቡበት የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ትግበራ፣ የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ እና የስታርታፕ አዋጅ ሥራ ላይ መዋላቸው የዲጂታል እምነትን አጠናክረዋል ብለዋል።

ቴክኖሎጂን በጤና፣ በግብርና እና በአገልግሎት ዘርፎች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

እስከ መስከረም 21 ቀን 2019 ዓ.ም በሚቆየው በዚህ መርሐ ግብር የፓናል ውይይቶች፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ፣ ሮቦቲክስ እና ስማርት ሲስተሞችን ጨምሮ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች ለዕይታ ይቀርባሉ።

Exit mobile version