አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) እየተጠናከረ የመጣው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የሁለትዮሽ ትብብር ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ድንበር ብቻ ሳይሆን ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነትና ወግ የሚጋሩ እንዲሁም ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብና ማህበራዊ ግንኙነት ያላቸው ጎረቤቶች ናቸው፡፡
የሀገራቱ የረጅም ጊዜ ግንኙነት በተለያየ ጊዜ ፈተና ቢገጥመውም፤ ውጣ ውረዶችን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ በማለፍ ዛሬ ላይ በቀጣናዊ ትብብርና የጋራ እድገት መርህ በአዲስ ምዕራፍ እየተጠናከረ ይገኛል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በሰላምና ፀጥታ ዘርፍ በተለይም ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ በጋራ ባከናወኗቸው ተግባራት እንደ አልሻባብ ያሉ የሽብር ቡድኖችን በማዳከም የሀገራቱን ብሎም የቀጣናውን የሽብር ስጋት ማስወገድ ችለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሰላም ለማስከበር ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሕይወት መስዋዕትነት ጭምር እውነተኛ አጋርነቷንና ወዳጅነቷን በተግባር አስመስክራለች።
የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር በአፍሪካ ሕብረትና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ መሠረት በአዲሱ የሶማሊያ የድጋፍና ማረጋጋት ተልዕኮ የሰላም ማስከበር ግዳጁን ቀጥሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው እለት ወደ አዲስ አበባ ለመጡት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼኽ መሐሙድ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች በሚያደርጉት ውይይት በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነትና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡
በሚኪያስ አየለ

