Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢሬቻ በዓል ለሁሉም ክፍት የሆነ ዓለም አቀፋዊ መድረክ ነው – አቶ ኃይሉ አዱኛ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢሬቻ በዓል በመልክ፣ በሀይማኖት፣ በቋንቋም ሆነ በማንነት ልዩነት የማያደርግና ለሁሉም ክፍት የሆነ ዓለም አቀፋዊ መድረክ ነው አሉ የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፡፡

መስከረም 23 እና 24 ቀን 2019 ዓ.ም የሚከበረውን የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓል ምክንያት በማድረግ 51ኛው የጉሚ በለል ውይይት “ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ሀሳብ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

አቶ ኃይሉ አዱኛ በመድረኩ ላይ እንዳሉት ፥ የኢሬቻ በዓል ከገዳ ሥርዓት የሚመነጭ የሰላም፣ የእርቅ፣ የአንድነትና የመተሳሰብ መገለጫ በመሆኑ የህዝቦችን አብሮነት በማጠናከር ለሀገራዊ መግባባት ከፍተኛ ሚና አለው።

በዓሉ በመልክ፣ በሀይማኖት፣ በቋንቋም ሆነ በማንነት ልዩነት የማያደርግና ለሁሉም ክፍት የሆነ ዓለም አቀፋዊ መድረክ ነው ብለዋል።

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓልም የሀገሪቱን ማንሰራራት በማወጅ ወደ ታላቅ ድል እየተሸጋገርን ባለንበት ወቅት የሚከበር ታላቅ በዓል በመሆኑ ከፍተኛ ስሜትና ትርጉም እንዳለውም አንስተዋል።

በበዓሉ እሴቶች አማካኝነት ከራሱ አልፎ ለሀገር የሚያስብና ፍቅር ያለው ትውልድ እየተገነባ እንደሚገኝ ገልጸው ህዝቡም ከሌሎች ብሔሮች ጋር ያለውን ወንድማማችነት በማጠናከር ለሀገር ከፍታ መስራት እንዳለበት ጥሪ አስተላልፈዋል።

በመድረኩ እየተሳተፉ የሚገኙ ምሁራን፣ አባ ገዳዎችና የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች የኢሬቻን እሴት፣ ሕግና ስርዓት በማብራራት ሀገራዊ መግባባትን ለማጠናከር የበኩላቸውን ማበርከት እንደሚጠበቅባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።

Exit mobile version