Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዓለም እየቀረጸችው ያለው አዲስ ታሪክ – ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀድሞው ዘመን የእድገት መለኪያ በሰፊ መሬትና በቁሳዊ ሀብትና ስኬት ብቻ የሚለካ ነበር፡፡ የአሁነ ግን በዕውቀት፣ በፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ልህቀት ፍጥነት ትመዝናለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት እንዳሉት ዕውቀት ችግር እስካልፈታ ድረስ በዕውቀት መስፈርት ውስጥ ሊታይ የሚያስችል ብቃት አይኖረውም።

በመሆኑም በዚህ መርህ መሰረት ያለንን እውቀት ወደ መሬት ወርዶ የህዝብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚፈታ፣ የሀገርን ሉዓላዊነት የሚያስከብር እና የዕለት ተዕለት ኑሮን የሚያቀል ኃይል ማድረግ ይገባል።

ዛሬ ላይ ኢትዮጵያም በዲጂታል ቴክኖሎጂው ዓለም ንቁ ተሳታፊና መሪ ለመሆን የምታደርገው ጉዞም ይህንን ፍልስፍና በተግባር እየተረጎመ ይገኛል።

በዚህም ቴክኖሎጂ በአሁኑ ወቅት በሲቪል ሰርቪስ፣ በሕግ ማስከበር፣ በጤና፣ በሚዲያ፣ በፋይናንስ፣ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች በስፋት አገልግሎት ላይ እየዋለ ነው።

ለአብነትም በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ሎጂስቲክስ የሚያጓጉዙ ድሮኖች እንዲሁም በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚንቀሳቀሱ ተዋጊ ጀቶች ጥቅም ላይ መዋላቸው የሀገራችንን ሉዓላዊነት ከማረጋገጥ ባለፈ የቴክኖሎጂ ልህቀት ደረጃችንን ማሳያ ናቸው።

ከዓመታት በፊት የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት በአፍሪካ በጣም ውድ ከነበሩት አንዱ ነበር፤ አሁን ላይ ግን ጤናማ ማሻሻያዎች በመደረጋቸው በአህጉሪቱ በዝቅተኛ ዋጋ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ማቅረብ ተችሏል ፡፡ ይህም የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሚያሳይ ነው።

በብሔራዊ መታወቂያ ፕሪግራም የሚሰጠው የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ከሁሉም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ጋር በማቀናጀት ቀልጣፋ አሰራርን ለመተግበር አስችሏል ። ይህም ቢሮክራሲን በመቀነስ ለዜጎች ፈጣን፣ ግልጽ እና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

ለወጣቶች በሚሊየን የሚቆጠሩ የዲጂታል ሥራ ዕድሎችን በማመቻቸት የፈጠራ አቅማቸውን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር የተቻለ ሲሆን በዚህም በርካቶች የሥራ ባለቤት እየሆኑ ይገኛል።

በስኬት የተጠናቀቀው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለኢትዮጵያ የዲጂታል ጉዞ መሰረት የጣለ ሲሆን እየተተገበረ የሚገኘው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም ሃገራችን በዘርፉ የምታደርገውን ጉዞ ወደ ከፍተኛ ምዕራፍ እንደሚሸጋግረው ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ልማት በአፍሪካ ቀዳሚ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንኑ በተመለከተ የኢትዮጵያ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጉዞ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮም ሁሉ የቴክኖሎጂ ምዕራፍም የአፍሪካውያን ኩራት መሆን የሚችል ነው ሲሉ ገልጸውታል።

በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከ“ቻት ጂፒቲ” ወይንም “ዲፕ ሲክ” ጋር ተመሳሳይነት ያለው፣ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን በስፋት የሚጠቀም “መላ” የተሰኘ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥርዓት ማበልጸግ ተችሏል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያው፣ በዓለም ደግሞ ሁለተኛው የሆነውን የመደመር ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት ሰፊ ዝግጅት እያደረገች ነው፡፡

ተቋሙ ሲጠናቀቅም ከሀገር ውስጥ አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል በማመቻቸት፣ ኢትዮጵያን የአህጉሪቱ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል ታሪካዊ ርምጃ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በፒኤችዲ ደረጃ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ትምህርት መሰጠት ተጀምሯል።

በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አጋርነት የተመረቀው ኤአይ ዩኒፖድ (AI UniPod) ማዕከል፣ ወጣቶች በሮቦቲክስ፣ በዳታ ሳይንስና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ምርምሮች ላይ እንዲሰማሩ ትልቅ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ፈጥሯል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የዲጂታል ጉዞ የነገን ዐሻራ በድምቀት የማኖር የድልና የተስፋ ጉዞ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ባበሰሩበት ወቅት እንዳሉት ተደራሽነትን ማስፋት፣ እኩል እድል መፍጠር እና በዜጎችና ተቋማት መካከል መተማመንን ማጎልበት የዘርፉ ቁልፍ ትልሞች ናቸው።

በሰለጠነ የሰው ኃይል ላይ የተመሰረተችውና በቴክኖሎጂ የዘመነችው አዲሷ ኢትዮጵያ፤ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ተወዳዳሪነት ከዕለት ወደ ዕለት እየጎላ መምጣቱ የማይቀር እውነት ነው።

በሶስና አለማየሁ

Exit mobile version