አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ጃፓን የኢትዮጵያን የሩዝ ምርት ዘርፍ ማዘመን የሚያስችል የ375 ሚሊየን ብር የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ እና በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ተፈራርመዋል።
አቶ አህመድ ሺዴ በዚህ ወቅት÷ የግብርና ዘርፍ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን፣ ለምግብ ዋስትና እና ለገጠር ብልጽግና ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ምርታማነትን ማሳደግ፣ የአርሶ አደሮችን ኑሮ ማሻሻል እና ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የሚመራ የግብርና ሽግግርን ማፋጠን ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ እና ጃፓን የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ ነው ማለታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

