አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የንግድ ስርዓትን ለማጠናከርና ብልሹ አሰራርን በማረም ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አውድ ለመፍጠር እንሰራለን አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ፍቅሬ አማን፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት በዛሬው ዕለት እያካሄደው በሚገኘው 7ኛ የምርጫ ዘመን መስራች ጉባዔ አቶ ፍቅሬ አማንን ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሰይሟል፡፡
ርዕሰ መስተዳደሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ክልሉ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ለዜጎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ምላሽ በመስጠት ረገድ በርካታ አዎንታዊ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት በቀጣይ አምስት ዓመታት የግብርና ዘርፉን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማስፋት እንዲሁም የክልሉን ኢኮኖሚ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም ትምህርት ቤቶችን በአደረጃጀት፣ በሰው ሀብትና በመሰረተ ልማት በማጠናከር የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ በትኩረት የሚሰራበት ዘርፍ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከዋና ተልዕኳቸው ባሻገር በየእርከኑ የሚገኙ የትምህርት ተቋማትን በግብዓት፣ በስልጠናና በምርምር እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በቤተልሄም ግርማ

