Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለሉዓላዊነትና ለብሔራዊ ደህንነት መረጋገጥ የተወሰዱ ወሳኝ ርምጃዎች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በኤርትራ እና ግብፅ ዲፕሎማቶች ላይ ያሳለፈችው ውሳኔ የሀገርን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ደህንነት ለማረጋገጥ የተወሰደ ወሳኝ ርምጃ ነው፡፡

ኢትዮጵያ «ቅድሚያ ለጎረቤት» በሚለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መርህ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር በማጠናከር ላይ ትገኛለች።

በመከባበርና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ የጎረቤት ግንኙነትን በማጠናከር የጋራ እድገትን እያረጋገጠች ሲሆን፤ ጎረቤት ሀገራትም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት አክብረው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ይሁን እንጂ እንደ ኤርትራ እና ግብፅ ያሉ ሽብር ጠማቂ ሀገራት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ደህንነት ለማናጋት ዲፕሎማቶቻቸውን ለሽብር ተልዕኮ ሲያሰማሩ ቆይተዋል፡፡

ቀደም ሲል የኤርትራ መንግሥት ከአልጀርሱ ስምምነት ውጭ በሁለቱ ሀገራት አዋሳኝ ድንበር አካባቢ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የጣሰ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በሌላ በኩል ግብፅ የዓባይ ወንዝን በብቸኝነት የመጠቀም አባዜዋ በውሃ ስምምነት ማዕቀፍ ከመደራደር ይልቅ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ ውስጥ ለማሳጣት ከምታደርገው ሙከራ ባለፈ የእጅ አዙር ጦርነቶችን ስታደርግ ቆይታለች፡፡

የግብፅ እና ኤርትራ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ቀጣናዊ አማፂያንን እና የታጠቁ ቡድኖችን በመደገፍ ኢትዮጵያን የግጭት መናኸሪያ ለማድረግ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

ከሀገራቱ ብሔራዊ ጥቅም ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ አለመግባባቶች በዲፕሎማሲ አግባብ እንዲፈቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ተዳጋጋሚ ጥሪዎችን ቢያቀርብም፤ ሀገራቱ ግን ለኢትዮጵያ ከሰላም ጥሪ በተቃራኒ እኩይ ተግባራቸውን አስቀጥለው ቆይተዋል፡፡

ከበርካታ የሰላም ጥሪዎችና ትዕግስቶች በኋላ ኢትዮጵያ በአስመራ የሚገኘው ኤምባሲዋ እንዲዘጋ ውሳኔ ማሳለፏን በትናንትናው እለት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች፡፡

በተጨማሪም 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶችና አንድ የግብፅ ዲፕሎማት በ48 ሰዓት ውስጥ አዲስ አበባን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፋለች፡፡

የ1961ዱ የቪየና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ኮንቬንሽን ሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነቶቻቸውን በሰላም፣ ሉዓላዊነትን በማክበርና በጋራ መከባበር ላይ ተመስርተው ሊያከናውኑ እንደሚገባ ያስገነዝባል፡፡

በዚህም መሰረት አንድ ዲፕሎማት ወይም የዲፕሎማሲ ሚሲዮን (ኤምባሲ) በተቀባዩ ሀገር ላይ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ሲፈጥር ወይም የጸጥታ አደጋ ሲሆን፤ ስጋቱን ለማስወገድ ሀገራት ራሳቸውን ለመካለከል የሚያስችላቸውን ርምጃዎች እንዲወስዱ ይፈቅዳል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው እንዳስታወቀው÷ ኢትዮጵያን ለቅቀው እንዲወጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው የግብፅ እና የኤርትራ ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በሚጥስና ብሔራዊ ደህንነቷን ስጋት ውስጥ የሚያስገባ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር፡፡

የውጭ ሀገር ዲፕሎማት ወይም የኤምባሲ ባልደረባ የተቀባይ ሀገርን ህግ ሲጥስ ወይም የብሔራዊ ደህንነት ስጋት በሚሆኑ ተግባራት ውስጥ ሲሳተፍ በቪየና ኮንቬሽን አንቀጽ 9 መሰረት ተቀባዩ ሀገር ማንኛውንም ዲፕሎማት የማባረር መብት አለው፡፡

ኢትዮጵያ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንዲሁም በሰላምና ደህንነት ዙሪያ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ሁሌም ቁርጠኛ ናት፡፡

ሰላም እና እድገቷን ለማይፈለጉ ኃይሎች ግን ዓለም አቀፋዊ ህጎችን መስረት ባደረጉ መልኩ ሉዓላዊነቷንና ብሔራዊ ደህንነቷን ለማረጋጋት ርምጃ መውሰዷን አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version