Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሚኒስቴሩ በባሕር ዳር ከተማ የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታን አስጀመረ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ትምህርት ሚኒስቴር በባሕር ዳር ከተማ የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታን አስጀመረ።

በግንባታው ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር)፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) እና ሌሎችም የክልል እና የባሕር ዳር ከተማ ከፍተኛ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በዚሁ ወቅት ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር) የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ጠንካራ ስነምግባር ያላቸውና በእውቀት የበለጸጉ የሃገር ተስፋዎችን ለማፍራት ወሳኝ ናቸው ብለዋል።

ሚኒስትሩ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ በ 12 ሺ ካ.ሜ ላይ ያረፈ እና 1 ሺህ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ያለው የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታን አስጀምረናል ነው ያሉት።

በዚህ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች የመጡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንደሚማሩ ጠቁመው አዲሲቷን ኢትዮጵያ በእውቀትና በችሎታ ላይ የምትመሰረተው በትምህርት ነው ብለዋል።

የትምህርት ቤቱ ግንባታ በ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ እንዲካሄድ የገለጹት ሚኒስትሩ ግንባታው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ብለዋል።

ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በክልሉ ውስጥ በተከሰተው ግጭት ምክንያት የትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር ያስታወሱት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን ወርቅነህ በበኩላቸው የሚገነባው አዳሪ ትምህርት ቤት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር በክልሉ ውስጥ ሌሎች 45 የመልሶ ግንባታ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 4 ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ 154 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ለትምህርት ቤቶች የሚያገለግሉ 306 ዘመናዊ የውሃ ታንከር ግንባታዎች በአማራ ክልል ውስጥ ማከናወኑ በመርሃ ግብሩ ተገልጿል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በደሳለኝ ቢራራ

Exit mobile version