Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መንገድ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በውጭ ጉዳይ ግንኙነት ታሪክ ውስጥ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ከቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ እውነታዎች ጋር እያጣጣሙ መጓዛቸው የህልውናና የዕድገት መሠረት ነው።

የመደመር ፍልስፍናን መሠረት ባደረገው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እየተመራች የምትገኘው ኢትዮጵያም ባለፉት ዓመታት በዲፕሎማሲው መድረክ ከቀድሞው ተጽዕኖ ተቀባይነት ወጥታ የራሷን አጀንዳዎች በልበ ሙሉነት የሚቀርጽና የሚያስፈጽም ከፍታ ላይ ደርሳለች።

በጋራ ተጠቃሚነትና በመግባባት ላይ የተመሠረተው ይህ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ በርካታ ድሎችንና ስኬቶችን አስመዝግቧል።

ኢትዮጵያ የዓለምን የኢኮኖሚና የጂኦ-ፖለቲካ እየቀየሩ ካሉት ሀገራት ስብስብ ከሆነው ብሪክስ ጋር መቀላቀሏ ስኬታማ ዲፕሎማሲያዊ ምዕራፍ ነው።

ኢትዮጵያ የብሪክስ ሙሉ አባል መሆን መቻሏ ስትራቴጂካዊ ቦታዋን ከማረጋገጡም በላይ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና የንግድ አውታሮች ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲዋቀሩ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንድትሆን አድርጓታል።

ኢትዮጵያ የፓን-አፍሪካኒዝም እምብርት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ መሥራች እንደ መሆኗ መጠን ለአህጉሪቱ ሰላም፣ ፀጥታና ውህደት የምታበረክተው አስተዋጽኦ የላቀ ነው።

በአህጉሪቱ በተለያዩ ቀጣናዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ ግጭት የተፈጠረባቸውን አካባቢዎች ሰላም ለማስከበርና የንግግር መድረኮችን ለማመቻቸት ሀገራችን ሁሌም ግንባር ቀደም ሚና ትጫወታለች።

ከአጎራባች ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት በጎረቤት ፍቅር፣ በንግድ ልውውጥ፣ በኃይል ትስስር እና በትራንስፖርት መረብ የተሳሰረ በመሆኑ ቀጣናዊ ውህደቱን በእጅጉ አጠናክሮታል።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋዎቿን ለሕዝቦቿ ልማት ስትጠቀም ሁልጊዜም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጉዳት የማያስከትል የጋራ ተጠቃሚነት መርህን አጥብቃ በመያዝ፣ በውይይትና በድርድር ችግሮችን ለመፍታት ያላት ቁርጠኝነት በዲፕሎማሲው ዓለም ትልቅ ክብር አትርፎላታል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም ለቀጣናው ትብብር ማሳያ በመሆን እየሰራ ይገኛል።

የመደመር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የኢኮኖሚ ትስስርን ማዕከል ያደረገ ነው። ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የምታደርጋቸው ጥረቶች፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የንግድ አጋርነቷን ማስፋፋቷ የኢኮኖሚዋን እድገት በእጅጉ የሚደግፍ ነው።

በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የኢትዮጵያ አቋም ሁልጊዜም የሉዓላዊነት ክብርን የተላበሰ፣ የቅኝ አገዛዝ ቅሪቶችን የሚቃወም እና የታዳጊ ሀገራትን ፍትሃዊ ጥያቄ የሚያስተጋባ ነው።

ኢትዮጵያ የራሷን ጉዳይ በራሷ የመወሰን ጽኑ አቋሟን በተግባር በማሳየቷ፣ በአጋሮቿ ዘንድ የላቀ እምነትና አክብሮት ማትረፍ ችላለች።

የመደመር መንግሥት በዲፕሎማሲው መስክ ያስመዘገባቸው ድሎች ጊዜያዊ ስኬቶች ሳይሆኑ ከጠንካራ ሀገራዊ ግንባታ ከሰላም ጥረቶች እና ከዘላቂ ልማት ፍላጎት ጋር የተሳሰሩ ስትራቴጂካዊ ምዕራፎች ናቸው።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ተሰሚነት እያደገ መምጣቱ የነገዋን የበለጸገች ሀገር እውን መሆን በግልጽ አመላካች ነው።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በሶስና አለማየሁ

 

Exit mobile version