አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር በወሰን ድንበር ብቻ የምትታጠር፤ የቆዳ ስፋት ወይም በካርታ ላይ የምትቀመጥ ምልክት ብቻ አይደለችም።
ሀገር በሕዝቦቿ የጋራ ሕሊና፣ በመደጋገፍ፣ በተጋሩት ታሪክና ወደፊት አብሮ ለመኖር ባላቸው የማይወላውል የጋራ ቃል ኪዳን ላይ የምትቆም ሕያው አካል ነች።
የሰው ልጅ በታሪኩ እንደተገነዘበው፣ ያልተግባባና የጋራ ማዕከል ያጣ ሕዝብ ለውጭ ጠላት ተጋላጭ፤ ለውስጥ መበታተን ደግሞ ቅርብ ይሆናል።
የታዋቂው የእንግሊዝ ፖለቲካ ፈላስፋ ቶማስ ሆብስ፤ ሰዎች የጋራ መግባባትና ሕጋዊ ማዕቀፍ ማበጀት ውስጥ ሳይገቡ በሚኖሩበት ጊዜ ሕይወት “ብቸኛ፣ ድሃ፣ አሰልቺና አጭር” ትሆናለች ይላል።
ሀገር የምትጸናው ሕዝቦቿ በነጻነት ተነጋግረው፣ ልዩነቶቻቸውን አከብረው፣ በጋራ መብቶቻቸውና ግዴታዎቻቸው ላይ ስምምነት ላይ ሲደርሱ ብቻ መሆኑን ያስረዳል።
ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ የታላቅነት፣ የነጻነት እና የታሪካዊ ሥልጣኔ ባለቤቶች መሆናቸውን ታሪክ ይመሰክራል።
ነገር ግን ይህንን ታላቅነት የሚመጥን ዘላቂ ሰላምና የጋራ ዕይታ መገንባት ባለመቻሉ፤ ያለፉት አያሌ ዓመታት ሀገራችንን ወደ ተደጋጋሚ የእርስ በእርስ ግጭት፣ የፖለቲካ ቅራኔ እና ሥር የሰደደ ጥርጣሬ ውስጥ ጥለዋታል።
አሜሪካዊው የፖለቲካ ምሁር ፍራንሲስ ፉኩያማ “Political Order and Political Decay” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደሚነግሩን፥ ጠንካራ ተቋማትና የጋራ ብሔራዊ ማንነት የሌላት ሀገር የቱንም ያህል የታሪክ ጥልቀት ቢኖራት ለውድቀት ትዳረጋለች።
ላለፉት አራት ዓመታት በሀገራችን የተካሄደው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ይህንን የታሪክ ስብራት ለመጠገን የተደረገ ትልቅ ጥረት ነው።
ኢትዮጵያውያን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ችግሮቻቸውን በግልጽ የመነጋገራቸው ምስጢር፤ ችግሩን ከሥር መሠረቱ ለማወቅና ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ የሚያስችል የመጀመሪያውና ዋናው መፍትሔ በመሆኑ ነው።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከምክክሩ የተገኙ የአጀንዳ ነጥቦችንና ምክረ ሐሳቦችን በትናንትናው ዕለት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንዲሁም ለፌደራልና ለክልል መንግሥታት በይፋ አስረክቧል፡፡
ይህም የንድፈ ሐሳቡን ምዕራፍ አጠናቆ ወደ ተግባር እና ውሳኔ የመሸጋገሪያ ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
ይህ ሰነድ ዝም ብሎ የወረቀት ክምችት አይደለም፤ ይልቁንም የአካታችነት ማረጋገጫ፣ በሰከነ መንገድ ቅደም ተከተል ያስቀመጠ የጋራ ፍኖተካርታና የቀጣዩ ትውልድ ስጦታ ነው።
የደቡብ አፍሪካውን የእውነትና የእርቅ ኮሚሽን ያስተባበሩት ዴስሞንድ ቱቱ “No Future Without Forgiveness” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳሉት፥ ያለፈውን ታሪክና ቁስል በግልጽ ተነጋግሮ መጋፈጥ ካልተቻለ ያለፈው ታሪክ የወደፊቱን ጊዜ ይበላዋል።
ኢትዮጵያም ያከናወነችው የምክክር ሂደት ያለፈውን ቁስል በውይይት በማከም ወደፊት የመራመድ ጥበብ ነው።
አሁን የተቀመጠው የሰነድ ርክክብ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ፍሬ ማፍራት መጀመሩን ያበስራል፤ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ከፍታ እንጂ ውድቀቷን የሚያመጣ ነገር አይኖርም፡፡
ይህ ሲባል በሕዝቦች መካከል የተደረሰው መግባባትና የታየው የመደመርና የመደማመጥ ፍላጎት አስተማማኝ መሠረት ስለመጣሉ አመላካች ነው ማለት ነው፡፡
ሀገር የምትጸናው በተግባባ ማኅበረሰብ ነው፤ ይህ የተጀመረው የሰላም፣ የውይይትና የመግባባት ጉዞ በተግባር ተተርጉሞ ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቦቿ የሚገባትን የታላቅነት ስፍራ እንደሚያረጋግጥ ሙሉ እምነት አለን።
በታሪኩ ለገሰ

