Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሲነኩት የሚፋጅ፤ ሲገፉት የሚጸናው ኢትዮጵያዊነት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያዊነት ሲነኩት የሚፋጅ፣ ሲገፉት የሚጸና ተራራ ነው። የታሪክ ማህደርን ቢገልጡ የዚህችን ሀገር ክብር ረግጦ ያለፈ፣ ማንነቷንም አሸንፎ የተሻገረ ኃይል የለም።
ይህ የአይበገሬነት ምሥጢር ዛሬም በደምና በአጥንት ቃል ኪዳን ታትሞ፣ ከምድር እስከ አየር የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ በተቆጣጠረው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ክንድ ላይ ደምቆ ይገኛል።
ይህንኑ ታሪካዊ ፅናት ሰንቆ የቆመው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ብሔራዊ ጥቅም፣ ሉዓላዊነትና የሕዝብ ደህንነት በማስከበር ረገድ ግንባር ቀደም ሚናውን በብቃት እየተወጣ ነው።
በተለይም ሀገራዊ አንድነትን ለመሸርሸርና ሉዓላዊነትን ለመድፈር የሞከሩ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ባዳዎች፣ በሠራዊቱ የማያወላውል ወታደራዊ እርምጃ ተደምስሰዋል፤ የጥፋት ሴራቸውም ከንቱ ሆኗል።
ሠራዊቱ በተቀናጀ የስትራቴጂክ ርምጃ፣ ጠላት የመሸሸጊያ ቀዳዳ አጥቶ በድንጋጤ “ጨርቄን ማቄን” ሳይል እንዲፈረጠጥ ከማድረግ ባለፈ፤ የሀገርን ሰላም ለማወክ የሚመጡ ማዕበሎችን ሁሉ ወደ ኋላ በመመለስ የሀገሪቱ የመጨረሻው ፅኑ ምሽግ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል።
ከሰሞኑ ኢትዮጵያን በታሪካዊ ጠላቶቿ የጥቅም ተላላኪ በሆኑ ቅጥረኞች አማካኝነት በሁሉም አቅጣጫ ለመክበብና ለመተናኮል የተሸረበው አደገኛ የሴራ ድር፣ በዚህ የሉዓላዊነት ዘብ እና ብረት ለበስ ክንድ ተበጣጥሷል።
ኢትዮጵያን አቅም አሳጥቶ ለባዕዳን ፍላጎት ለማንበርከክ ሌት ተቀን የደከሙ ኃይሎች፣ የመከላከያ ሠራዊቱን ስልታዊ ጥንካሬና የማይናወጥ ህብረት መቋቋም አቅቷቸው ዕቅዳቸው ሁሉ መክኖ ቀርቷል።
ይህ ድል፣ የኢትዮጵያን ክብር ለመድፈር የሚነሱ ማናቸውም ቅጥረኞች ትምህርት ሰጥቷል።
ይህ የጦር ሜዳ ጀግንነት በተለመደ ወኔ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ልህቀት ጋር በጥልቅ ተዋህዷል።
ሠራዊቱ የስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽንና የሳይበር ደህንነት መዋቅሮችን በማጠናከር የጠላትን ዲጂታል ጥቃቶችና የስነ-ልቦና ጦርነቶች ከጥንስሱ ያከሽፋል።
ከዚህ ዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ ጎን ለጎንም፣ የቀኑ ሃሩርና የሌሊቱ ቁር ሳይበግረው፣ አስቸጋሪ መልክዓ ምድሮችን አሸንፎ የሀገሪቱን ድንበር በንቃት ከመጠበቅ አልፎ በብሔራዊ ልማት ላይ ትልቅ አሻራ እያሳረፈ ይገኛል።
በተለይም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችን ምሰሶ የሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ካንዣበቡባቸው ማናቸውም የደህንነት ስጋቶች በጥንካሬ በመከላከል የልማት ዋስትናነቱን በተግባር አረጋግጧል።
የዚህ ሁሉ ኃያልነትና ያልተቋረጠ የድል ምሥጢር የሚመነጨው ደግሞ ሠራዊቱ ከተገነባባቸው እሴቶችና ካለው ጠንካራ ሕዝባዊ መሠረት ነው።
ሠራዊቱና ሕዝቡ ፍጹም የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች በመሆናቸው፣ የጥፋት ኃይሎች በመካከላቸው ሊፈጥሩ የሞከሩት የከፋፋይነት ወጥመድ ሁሉ በተቋሙ ሕዝባዊ ባህሪና ስነ-ልቦናዊ ፅናት ምክንያት መክኗል።
ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም ቅድሚያ መስጠትና የተሟላ ሙያዊ ስብዕናን መላበስ የዚህ አሸናፊ ኃይል ዋነኛ መገለጫዎች ናቸው።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ባለው አርበኝነት ላይ ዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ደምሮ የኢትዮጵያን ታላቅነትና ሉዓላዊነት በፅኑ ክንዱ ማስከበሩን አጠናክሮ ይቀጥላል።
ይህ የማይበገር ኃይል የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር ተልዕኮውን የመፈጸም ብቃቱ ፍጹም አስተማማኝ ሲሆን፤ በእርሱ ፅኑ ዘብነት የኢትዮጵያዊነት ታላቅነት ምንጊዜም ከፍ ብሎ ይኖራል።
በኃይለኢየሱስ መኮንን
Exit mobile version