Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዓድዋ የልጅ ልጅ ያያል- ቀይ ባህር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አንዳንድ ታሪኮች በተፈጸሙበት ቀን አያልቁም። አንዳንድ ድሎችም በተደረገው ጦርነት ውስጥ ተወስነው አይቀሩም። የአንድ ትውልድ ድል ለሌላ ትውልድ ራዕይ ይሆናል። የአንድ ትውልድ መስዋዕትነት ለሌላው ትውልድ የመነሻ መሠረት ይሆናል። ዓድዋም እንዲሁ ነው።
ዓድዋ…
ዓድዋን ዛሬ የምናስበው እንደ 1888 ዓ.ም. በተደረገ አንድ ታላቅ ጦርነት ብቻ ከሆነ፣ የታሪኩን ግማሽ ብቻ ነው የተረዳነው። የዓድዋ ትልቁ ትርጉም ኢትዮጵያ የራሷን ዕድል በራሷ የመወሰን መብቷን ማስጠበቋ ነው። ያ መብት ደግሞ በጦር ሜዳ ብቻ አልቀረም።
ዓድዋ የነፃነትን መሬት አስጠበቀ፤ አባይም በዚያ መሬት ላይ ፈሰሰ። መሬቷን፣ ውሃዋን፣ ዕውቀቷንና የሕዝቧን ኃይል ለራሷ ዕድገት የማዋልን አደራ ጥሎ አለፈ።
ከዚህ አንፃር ሲታይ፣ ዓድዋ ከጦር ሜዳ ወጥቶ ጥያቄ ይፈጥራል። ጥያቄውም ከዓባይ ጋር ይገናኛል። አባይ ከኢትዮጵያ የሚነሳ ውሃ ብቻ አይደለም። የተፈጥሮ ሀብት፣ የልማት ዕድልና የትውልድ ተስፋ ነው። ስለዚህ የዓባይ ጉዳይ የውሃ ብቻ አይሆንም። የሉዓላዊነት፣ የልማትና የወደፊት ጥያቄ ይሆናል።
ገ/ጻድቅ ደገፉ ናይል በተሰኘ መጽሐፋቸው ከዓድዋ ጦርነት 5 ዓመት በፊት በብሪታንያና ጣሊያን መካከል የተፈረመው ፕሮቶኮል (1883) ጣሊያን ኢትዮጵያን ከወረረች በኋላ(ጀግኖቹ ከንቱ አስቀሩት እንጂ) እጇን በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ እንደማታስገባ ውል ገብታለች። እዚህ ላይ ዓድዋና አባይን በአንድ የታሪክ መስመር ላይ እናገኛቸዋለን።
ዓድዋ የሀገርን ነፃነት አስጠበቀ፤ ያ ነፃነት ደግሞ አባይን ለራስ ልማት የማየት መብትን አጠናከረ። በዚህ ተምሳሌታዊ ትርጉም፣ ዓድዋ አባይን አዳነ፤ ልጅ ህዳሴ ግድብ ተጸነሰ።
ህዳሴ ግድብ…
ውሃ በራሱ ልማት አይሆንም። የተፈጥሮ ሀብት ወደ ሕዝብ ተጠቃሚነት ለመቀየር ራዕይ፣ ዕውቀት፣ ቴክኖሎጂ፣ ካፒታልና የሕዝብ ተሳትፎ ያስፈልጋል። እናም ዓድዋ ልጅ ወለደ – የታላቁ ህዳሴ ግድብ።
ህዳሴ የአንድ ግድብ ስም ብቻ አይደለም። አባይን እንደ ተፈጥሮ ሀብት ተመልክቶ ወደ ልማት ለመቀየር የተነሳ ጥልቅ ሀሳብ ነው።
ዓድዋ የጠበቀው ነፃነት፣ ህዳሴ ደግሞ ያንን ነፃነት ወደ ልማት ለመቀየር የተነሳ ምኞት ነው። ስለዚህ የህዳሴ ግድብ የዓድዋ ድል ቀጥተኛ ውጤት ሆነ ማለት ነው። በዓድዋ የታየው አይበገሬ የአሸናፊነት መንፈስ ያረበበበት ሥራ። ሉአላዊነት።
ህዳሴ የሚያልመው ከግድቡ በላይ ነው። አንድ ግድብ በወንዝ ላይ ይገነባል ነገር ግን አንድ ሀገር የምትገነባው በርዕይ ነው። ስለዚህ ህዳሴን በኮንክሪት ግድቡ ብቻ መለካት አይቻልም። የህዳሴ ሐሳብ የኢትዮጵያን የልማት አድማስ ማስፋት ከሆነ፣ አድማሱ በአባይ ዳር አይቆምም። በሌላ አባባል ህዳሴ በተራው ቀይ ባሕርን ጸነሰ።
ቀይ ባሕር…
“ጸነሰ” የሚለውን ቃል እዚህ በተለየ ትርጉም እንጠቀምበት። ህዳሴ ቀይ ባሕርን በታሪካዊ ሁኔታ እንደወለደው ሳይሆን፣ የሀገርን የልማት እይታ ከውስጥ ወደ ውጭ እንዲያይ የሚያስገድድ አዲስ ምዕራፍን እንደ ጸነሰ ይወሰድ። ምክንያቱም ልማት በድንበር አይቆምም።
የኃይል ምርት ገበያ ይፈልጋል። ምርት መጓጓዣ ይፈልጋል። ንግድ ወደ ዓለም የሚወጣበት መስኮት ይፈልጋል። በዚህ የልማት ትስስር ውስጥ ቀይ ባሕር የራሱ ስፍራ አለው። ስለዚህ ከዓድዋ ጀምሮ የሚመጣው የሐሳብ ጉዞ እዚህ ላይ ይደርሳል፤ እና ህዳሴ አባት ይሆናል። ዓድዋም አያት
የዓድዋ ትውልድ የራሱን ጊዜ በደማቁ ጽፏል። እኛ የእነሱን ውጤት ተረክበን የራሳችንን ጊዜ እየገነባን ነው።
ልጆቻችን ደግሞ የእኛን ውጤት ይመለከታሉ። እነሱ ሲመጡ የዓድዋን ታሪክ ብቻ እንዳያነቡ፤ የዓድዋን ትርጉም እንዲኖሩት ማድረግ አለብን። ህዳሴን እንደ ግድብ ብቻ እንዳይወርሱ፤ እንደ የልማት ርዕይ እንዲወርሱ ማድረግ አለብን።
ቀይ ባሕርንም እንደ የዛሬ የፖለቲካ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ የምታየው የነገ የኢኮኖሚና የክልላዊ ትስስር አድማስ እንዲሆን እንፈልጋለን። ምክንያቱም የትውልድ ትልቁ ተልዕኮ ያለፈውን ታሪክ ማስታወስ ብቻ አይደለም። ያለፈው ትውልድ የጀመረውን ታሪክ በራሱ ዘመን ቀጥሎ፣ ለሚመጣው ትውልድ የተሻለ ምዕራፍ ማስረከብ ነው። ዓድዋ የነፃነት ምዕራፍ ከሆነ፣ ህዳሴ የልማት ምዕራፍ ነው፤ ቀይ ባሕር ደግሞ የሚቀጥለው አድማስ ነው።
…እና ዓድዋ የልጅ ልጅ ያያል።
የትናንት ድል የዛሬ ኃላፊነት ሲሆን፣ የዛሬ ሥራ ለነገ ትውልድ ብድር ይሆናል። ዓድዋ ህዳሴን ወለደ። ህዳሴ አድማሱን አስፋፍቶ ቀይ ባሕርን እንደ ቀጣዩ የሀገር ርዕይ አስተዋወቀ። እና ይህን ሁሉ የሚመለከተው ማን ነው? የልጅ ልጅ።
ዓድዋ — ነፃነት።
ህዳሴ — ልማት።
ቀይ ባሕር — አድማስ።
ዓድዋ የልጅ ልጅ ያያል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

 

በሠራዊት ከበበው
Exit mobile version