አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተተገበረው የ”መደመር” ፍልስፍና ዋና ዋና ግቦች አንዱ የመንግሥትን የአገልግሎት አሰጣጥን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ግልጽ ማድረግ ነው።
የመንግሥት መዋቅር ለዜጎች ምቹ፣ ፈጣን እና ከእንግልት የጸዳ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል በርካታ መዋቅራዊ እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ማሻሻያዎች ተካሂደዋል። እነዚህ የተከናወኑ ስኬታማ ሥራዎች የመንግስትን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ እያሸጋገሩት ይገኛሉ።
የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ከተከናወኑት ጥረቶች መካከል የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትልቅ ድርሻ አለው።
የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የዜጎችን ማንነት በዘመናዊ ባዮሜትሪክ ቴክኖሎጂ በማደራጀት በባንክ፣ በኢንሹራንስ እና በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ፈጣን፣ አስተማማኝ እና የተሳለጠ አገልግሎት እንዲኖር አስችሏል።
የግብር፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የትራፊክ ቅጣት እና የተለያዩ የአገልግሎት ክፍያዎች በዲጂታል የክፍያ አማራጮች ማለትም እንደ ቴሌብር፣ ሲቢኢ ብር እና ኦንላይን የባንክ ሥርዓቶች በኩል እንዲፈጸሙ በመደረጉ ጊዜና ወጪን በእጅጉ ለመቀነስ አስችሏል።
የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል አሰባስቦ ማቅረብና አሰራርን ማቃለል በዋናነት የተከናወነ ሌላኛው ሥራ ነው፡፡
የባለብዙ አገልግሎት ማዕከል የሆነው የመሶብ አንድ አገልግሎት ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር የገባ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች በተገነቡ ማዕከላት አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡
የንግድ ፈቃድ ማውጣት፣ ማደስ እና የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሂደቶች በኦንላይን ስርዓት እንዲከናወኑ በመደረጉ ኢንቨስተሮች እና ነጋዴዎች ባሉበት ሆነው አገልግሎት የሚያገኙበት አሰራር ተዘርግቷል።
በርካታ የፍትህ እና የሲቪል ምዝገባ አገልግሎቶች በዲጂታል ኔትወርክ ተገናኝተው በተለያዩ ማዕከላት ወይም በዲጂታል መንገድ ተደራሽ እንዲሆኑ ተደርጓል።
የዜጎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለማቃለል፣ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማዘመን እና የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማትን አካባቢ ምቹና ማራኪ ለማድረግ የኮሪደር ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
በተከናወኑ በርካታ የመዋቅርና የሰው ሀይል ግንባታ ሥራዎች የመንግስት መሥሪያ ቤቶች ተገልጋዮችን በክብር እና በቅልጥፍና የሚያስተናግዱበት አዲስ የአገልግሎት ባህል እንዲገነባ ተደርጓል።
የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን ለማዘመን እና ሌብነትንና ሙስናን ለመቀነስ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የኢንተርኔት የታክስ አስተዳደር ሥርዓት (የኢ-ታክስ) እና የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ ሥርዓቶች ተተግብረዋል። ይህም የግብር ከፋዩን እንግልት ከመቀነሱም በላይ ግልጽነትና ተጠያቂነትን አጠናክሯል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በመደመር እይታ ስር የጀመረችው የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ዘመናዊ፣ ቴክኖሎጂ መር እና ዜጎችን ማዕከል ያደረገ የመንግስት አስተዳደር ለመገንባት አስተማማኝ መሰረት ጥሏል።
አሰራሮችን በየጊዜው ይበልጥ በማዘመን ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎትን በማረጋገጥ በሁለንተናዊ ዘርፍ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡
በመልካም ፈቃዱ

