አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ከተሞች ከተማ የሚያስመስላቸውን መልክና አገልግሎት መላበስ ይገባቸዋል፡፡ ማህበረሰቡም የከተሜነትን የአኗኗር ባህልን መላበስ እንደሚገባው ይታመናል፡፡
የኮሪደር ልማት አካባቢን ውብና ፅዱ የማድረግን ዓላማ ብቻ ይዞ የተነሳ አይደለም፡፡ ይልቁንም ዜጎች የሚገባቸውን የተሟላ አገልግሎት ማግኘት አለባቸው በሚል መንፈስ የተቃኘ ነው፡፡
ዜጎች የሚገባቸውን አገልግሎትና ክብር ከሚያገኙባቸው መንገዶች አንዱ ጽዱና ምቹ የመኖሪያ ቦታ እንዲሁም ለፈጠራና ራስን ለማሳደግ የሚያስችል ከባቢ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኮሪደር ልማቱ የሀገራችንን ከተሞች ገፅታ እና የህዝቦችን አኗኗር በከፍተኛ ሁኔታ ለማሻሻል አግዟል፡፡
ዜጎች ይኖሩባቸው የነበሩ ጥራታቸውን ያልጠበቁ የመኖሪያ ቤቶችን አዘምኖ መስራትና ዘመናዊነት በተላበሰ መልኩ የህጻናት መጫወቻዎችን፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የኮሪደር ልማቱ ትሩፋቶች ናቸው፡፡ የትራፊክ ፍሰትን እና የሰዎችን እንቅስቃሴ ምቹ የሚያደርጉ ሰፋፊ መንገዶች፣ የእግረኛ እና የብስክሌት መስመሮች መሰራታቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አስገኝቷን፡፡
በኮሪደር ልማቱ ምክንያት በየጉራንጉሩ ጨለማን ተገን አድርገው የሚከሰቱ የዝርፊያ ወንጀሎች መቀረፋቸው ዜጎች በፈለጉበት ሰዓት መውጣትና መግባት የሚችሉበትን አመቺ የአኗኗር ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
ሀገር በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ብትሆን የልማት ጉዞዋን አብራ የምታስኬደው እንጂ ለነገ በይደር የምታቆየው አይደለም፡፡ ዛሬ ላይ በፈተናዎች ውስጥ እየታለፉ የተሰሩ ስራዎች ሁሉ ውጤታቸው ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገንም የሚሻገር ስኬት ነው፡፡
የከተሞች ኮሪደር ልማት ለኢትዮጵያውያን የኑሮ ዘይቤያቸውን ከመቀየር ባለፈ ፣ በዓለም የሀገራችንን ገፅታ ጭምር የቀየረ ስኬት ነው፡፡
ኢትዮጵያ በ2018 ብቻ ከ200 በላይ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችንም በማስተናገድ በርካታ የውጭ ሀገራት ዜጎች ወደ ሀገራችን እንዲመጡ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህም ሀገራችን የኮንፈረንስ ቱሪዝም እንዲጎለብት በማድረግ በቱሪዝም ዘርፉ የምታገኘውን ገቢ እያሳደገች ነው፡፡
ዘመናዊነትን የተላበሱ የመሰረተ ልማትና የመንገድ ግንባታዎች የትራንስፖርቱን ሁኔታ ያሻሻሉ እንዲሁም፣ ዜጎች ከዚህ ቀደም ወደ ስራ ቦታቸው ለመድረስ የነበረባቸውን የትራፊክ ፍሰት ችግርና መዘግየት ያስቀሩ ናቸው፡፡
በመሆኑም የኮሪደር ልማት ከተሞችን እንዲሁም የሚኖርባቸውን ማህበረሰብ ኋላ ቀር ከነበረው የማይመጥን የመኖሪያ ከባቢ ወደ ውብና ዘመናዊ ከተማነት ያሸጋገረ ትሩፋት ነው፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በቤተልሔም ግርማ

