Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

መጪዎቹ ታሪካዊ መስከረሞች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲሱ ዓመት፣ አዲስ ተስፋ እና አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚበሰርበት የኢትዮጵያውያን መስከረም ሁልጊዜም ልዩ ትርጉም አለው።
ከመጪዎቹ መስከረሞች የሚጠበቀው ግን ተራ የቀን መቁጠሪያ ሽግግር ብቻ ሳይሆን፤ ሀገሪቱ ከገጠሟት ውስብስብ ፈተናዎች ተሻግራ የማንሰራራት ዘመኗን የምታውጅበትና የብልጽግናዋን መሰረት በጸና አለት ላይ የምታኖርበት ወሳኝ የጉዞ አቅጣጫ ነው፡፡
በምርጫ የዜጎችን ይሁንታን ያተረፈው አዲሱ መንግሥት በህጉ መሰረትና በሕዝብ ሙሉ ቅቡልነት ምስረታውን አካሂዶ በዛሬው ዕለት በይፋ ስራ ሲጀምር፤ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አውድ የማረጋጋት ሚናውን አጠናክሮ ይቀጥልበታል።
መጪዎቹ አምስት መስከረሞች ቀደም ሲል የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ስራዎች የሚጠናቀቁበት እንዲሁም አዳዲስ የሚጀመሩበትና ፍሬ የሚያፈራበት ይሆናሉ።
ከመሰረተ ልማት እስከ ታላላቅ የኃይል ማመንጫዎች፣ ግብርናን ከማዘመን እስከ ወደብና ትራንስፖርት ትስስር እንዲሁም ከኢንዱስትሪ መስፋፋትና ዲጂታላይዜሽን ጋር ተያይዘው የተወጠኑት ታላላቅ ትልሞች ሀገሪቷን ወደ አዲስ የኢኮኖሚ ልዕልና ምዕራፍ ያሸጋግራሉ፡፡
ይህ ስኬት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን እውን ከማድረጉ ባሻገር፤ ለመጪው ትውልድ ጠንካራና ራሷን የቻለች ሀገር የመረከብ ተስፋን ያረጋግጣል።
በመሆኑም እነዚህ መስከረሞች የኢትዮጵያን ዳግም ማንሰራራት በይፋ የሚያውጁ የተስፋ ዘመናት ይሆናሉ።
እኚህ የስኬትና የተስፋ ዘመናት ግን መንገዳቸው አልጋ በአልጋ ላይሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ከየትኛውም የእድገትና የመትጋት ጉዞ ጀርባ ፈተናን የሚጋርጡ በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ አስጊ ሁኔታዎች ይጠበቃሉና፡፡
የሀገርን ሰላምና አንድነት ለማናጋት፣ የሕዝብን የእርስ በእርስ መስተጋብር የሚያሻክሩና የውጭ ጠላቶችን ፍላጎት በማስፈጸም የልማት ጉዞውን ለማስተጓጎል የሚሰሩ አካላት የሚፈጥሩት ስጋት ቀላል የሚባል አይሆንም።
ነገር ግን ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ሲያስመሰክሩት እንደኖሩት፤ በጽናትና በሀገር ፍቅር ስሜት እጅ ለእጅ በመያያዝ እንደሚሻገሩት ቅንጣት ጥርጣሬ አይኖርም፡፡
ሌላኛው ፈተና የጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች፣ የዓለም አቀፍ የነዳጅና የሸቀጦች ዋጋ መናር እንዲሁም ቀጣናዊ ግጭቶች በሀገራዊ ኢኮኖሚና የኑሮ ውድነት ላይ የሚያሳድሩት አሉታዊ ተጽዕኖ ትልቅ ውጫዊ ስጋት ነው።
መጪዎቹ መስከረሞች ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን ታላላቅ የልማት ስራዎች አጠናቅቃ አዳዲሶችን በማብሰር ወደ ብልጽግና የምትሸጋገርበትን የታሪክ በር የሚከፍቱ ወሳኝ ምዕራፎች ናቸው።
ነገር ግን ይህ ተስፋ እውን ሊሆን የሚችለው የሌብነትን እሾህ በመንቀል፣ የአፍራሽና ተላላኪ ኃይሎችን ሴራ በጥበብና በጽናት በመመከት እንዲሁም የኑሮ ውድነትን የሚያቃልሉ ስትራቴጂያዊ የኢኮኖሚ ርምጃዎችን ከመንግሥት ጋር በመሆን በመደገፍ ነው።
ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ማንሰራራትና ለአዲሱ ትውልድ ብሩህ ተስፋ፣ መጪዎቹ አምስት መስከረሞች የእውነትም የኢትዮጵያ ብልጽግና ማብሰሪያ ይሆናሉ።
በመልካም ፈቃዱ
Exit mobile version