Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያዊነት በፈተናዎች ያልተበገረውና በወረራዎች ያልተሰበረው ኢትዮጵያውያን በመደመር መንገድ ስለሚጓዙ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ፈተናዎች ያልበገሩትና የውጭ ወረራዎች ያልሰበሩት ኢትዮጵያዊነት የተገኘው ኢትዮጵያውያን በመደመር መንገድ ስለሚጓዙ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
የአዲሱ የመደመር መንግሥት ምሥረታ እና የኢፌዴሪ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን የምክር ቤቱ መመስረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ተካሂዷል።
ምክር ቤቱ በስብሰባው ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በስብሰባው ባደረጉት ንግግር ÷ በአንድ እንቅፋት አንዴ መመታት ተፈጥሯዊ ቢሆንም ደጋግሞ መመታት ግን የጤና አይደለም ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር ቀድሞ አለመዘጋጀት የሚያስከፍለውን ዋጋ ለማየት የጣሊያን ዳግም ወረራ መለስ ብሎ መቃኘትና ተገቢ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በዓድዋ ጦርነት አንገቱን ደፍቶ የተመለሰው ወራሪ ኃይል አራት አስርት ዓመታት አንገት ቀና በሚያደርግ ዝግጁነት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
በአንጻሩ ከዓድዋ ድል ማግስት አሸልበን በመቆየታችንና ባለመዘጋጀታችን አላስፈላጊ ዋጋ ከፍለናል ነው ያሉት፡፡
ባልተዘጋጁበት ግንባር እንደመግጠም ያለ ክፉ ቀን የለም፤ የከፋው ቀን ተመልሶ እንዳይመጣ ዛሬም ዳግም እንጠይቃለን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ዛሬስ ኢትዮጵያ ምን ያህል ተዘጋጅታለች፣ አንዳችን የሌላችንን እንከን መንቀስ ትተን ዐይናችን ምን ያህል ወደ ወጪ ያማትራል ሲሉም አንስተዋል፡፡
ቀጣናችን እየተቀየረ ነው፤ ጎረቤቶቻችን፣ የአፍሪካ ቀንድ፣ ቀይ ባሕር አካባቢ፣ የፋርስ ባሕረ ሰላጤ የመካከለኛ ምስራቅ በሁሉም አቅጣጫ በለውጥ ማዕበል እየተጎበኘ ነው ብለዋል፡፡
እኛ ደግሞ በአስገራሚውና በአስፈላጊው ምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ላይ እንገኛለን፣ ይህም ፈተናም እድልም እንዳለው አብራርተዋል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ የሚነሳ የለውጥ ዝናብ እኛን ሳያገኘን ያልፋል ማለት ዘበት ነው፤ ፈለግንም አልፈለግንም የዚህ ከባቢ ለውጥ እኛንም ይጎበኘናል፤ ለዚህም ታሪክ ምስክር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ዛሬ ያለንበት ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ በፍጥነት እየተለዋወጠ ነው፤ በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ ጠንክረን መጋፈጥ ከቻልን እንደምናሸንፍ እሙን ነው፤ ደክመን ከተገኘኝ ደግም ሽንፈት የምንጎነጨው ጽዋ ይሆናል ነው ያሉት፡፡
ሥርዓት በአንድ ጀምበር ተገንብቶ አያልቅም፤ ይልቁንም ሥርዓት በሒደት የሚፈጠር ትዕግስትና ተጋትን እኩል የሚጠይቅ ጥበብና ስክነትን አጣምሮ የያዘ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የነበሩ ሥርዓቶች ለሀገራችን ችግር ለሌሎች ተቀድዶ በተሰፋ እሳቤ ሊፈቱ ይሞክሩ ነበር፤ ይህም ለበርካት ችግር አጋልጦን ቆይቷል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስሩ በንግግራቸው፡፡
እኛም የኢትዮጵያን ችግር ሊፈታ የሚችለው እሳቤ ምንድን ነው? ብለን ፈትሸናል፤ በዚህም የኢትዮጵያን ችግር መፍታት የሚችል ሀገር በቀል እሳቤ አግኝተናል፤ ይህም “መደመር” ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ፈተናዎች ያልበገሩት፣ የፖለቲካ ሊሂቃል ያልከፋፈሉትና የውጭ ወረራዎች ያልሰበሩት ኢትዮጵያዊነት ሊገኝ የቻለው ኢትዮጵያውያን በመደመር መንገድ ስለሚጓዙ ነው ሲሉም የመደመር እሳቤ ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ የሚሰጥ እሳቤ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
Exit mobile version