Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሚጠብቀንን ፈተና መሻገር የምንችለው እንደ ወንድማማች ተያይዘን እኩል መራመድ ስንችል ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) እንደ ሀገር የሚጠብቀንን ፈተና መሻገር የምንችለው እንደ ወንድማማች ተያይዘን እኩል መራመድ ስንችል ነው  አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡

የአዲሱ የመደመር መንግሥት ምሥረታ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

ምክር ቤቱ በጉባዔው ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በጉባዔው ባደረጉት ንግግር÷ ዛሬ ዘመኑ ተቀይሯል፤ ነገሮች እንደ ድሮው አይደሉም፤ ሀገራዊ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች በፍጥነት ይለዋወጣሉ ነው ያሉት፡፡

እንደ ሀገር የሚጠብቀንን ፈተና መሻገር የምንችለው እንደ ወንድማማች ተያይዘን እኩል መራመድ ስንችል ነው ብለዋል፡፡

አይገመቴነት የዘመኑ ዋነኛ መገለጫ እየሆነ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ÷ ቋሚ አሰላለፍ ማየት ብርቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ጥቁርና ነጩ ባለየለት ግራጫ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አውድ ውስጥ እንገኛለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ታሪክ ወደየትኛው አዲስ ምዕራፍ እንደሚያደርሰን በግልጽ በማይታወቅበት መንታ መንገድ ላይ መሆናችን እሙን ነው
ብለዋል፡፡

አዲስ አነገር እዳም፥ ምንዳም አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ እዳ እና ምንዳው ግን ለሁሉም እኩል እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

መጪው ዘመን ቀድመው አስበው፤ የሚመጣውን አዲስ ነገር ገምተው በተጠንቀቅ ለሚጠብቁ ብርቱዎች ምንዳው ብዙ ነው፤ በአንጻሩ ለተዘናጉት ደካሞች ደግሞ እዳው እልፍ ነው ብለዋል፡፡

ለሀገራችን የሚበጀውን መንገድ መርጦ መከተል የዚህ ትውልድ ታላቁ አደራ ይሆናል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version