አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት ሁሉን አቀፍ የማህበረሰብ ተሳትፎ መንገድን በመከተሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጨባጭ ዕድገት እንደሚዘገብ አስችሏል አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፡፡
የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 7ኛ የስራ ዘመን 1ኛ ዓመት የጋራ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ የሁለቱ ምክር ቤት ተመራጭ አባላት በተገኙበት ተካሂዷል።
ፕሬዚዳንት ታዬ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ የመላው ሕዝቡ ተሳትፎ ማደጉ በመንግሥት እና በሕዝቡ ትብብር የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ፕሮግራሞች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻሉን ገልጸዋል።
ለአብነትም የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ጉልህ በሆነ መንገድ ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በአጭር ጊዜ ውስጥ አስደናቂ ውጤት ያስመዘገበው የከተሞች የተቀናጀ የዝምንና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶችን ማንሳት ይቻላል ነው ያሉት።
እነዚህ ስኬቶች መንግሥት ያወጣቸውን ዕቅዶች ለመፈጸም መትጋቱን እንዲሁም ማህበረሰቡ ያለውን ሁሉ መስጠቱን እንደሚያረጋግጡ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የዕድገት ግስጋሴ በሚቆጠሩና በሚታወቁ አመላካቾች ማሳየት እንደሚገባ ገልጸው፤ የ2018 ዓመታዊ የሰብል ምርት በ2011 ከነበረው 335 ሚሊየን ኩንታል ወደ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ኩንታል ምርት መድረሱ አስረድተዋል።
የወጪ ንግድ ገቢ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 11 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ማስመዝገቡ እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ካለፈው ዓመት ስኬቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።
እንዲሁም የብድር አቅርቦት ወደ 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር ማደጉ፣ የዋጋ ግሽበት በግንቦት ወር 2018 በ13 ነጥብ 4 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉ፣ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ገቢ 1 ትሪሊየን 980 ቢሊየን ብር መድረሱ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ስኬቶች ናቸው ነው ያሉት፡፡
በአቤል ነዋይ

