አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት፣ ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ ዘመኑን የዋጀ እና ጠንካራ መከላከያ ሠራዊት መገንባት ያስፈልጋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች መቋቋም ብቻ ሳይሆን ሊመጡ የሚችሉ ስጋቶችን አስቀድሞ በመለየትና በመከላከል ላይ የተመሠረተ የዝግጁነት ባህል እየገነባ ይገኛል።
የዚህ ግንባታ መሠረት ዘመናዊ፣ በወታደራዊ ሥነ ምግባር የታነጸ፣ ሁሌም ዝግጁ፣ ብቁና ንቁ የሆነ ኃይል መፍጠር ነው።
የጦርነት ባህሪ በፍጥነት እየተለወጠ ባለበት በአሁኑ ዘመን የመከላከያ ኃይል ከውጊያ አቅም ባሻገር ቴክኖሎጂን፣ መረጃን፣ የስለላ አቅምንና ፈጣን ውሳኔ የመስጠት ብቃትን በማጣመር መሰማራት ይጠበቅበታል።
በዚህ መሠረት ሠራዊቱ በየአውዱ የመሰማራት አቅምና ቁመና እንዲኖረው የሚደረገው ግንባታ ከመሣሪያና ከወታደራዊ ቴክኖሎጂ ብቻ የሚመዘን አይደለም።
በተግባር የሚሰማራ ሠራዊት ፈጣን ምላሽ የመስጠት፣ በተለያዩ የጦርነትና የደህንነት አውዶች የመስራት፣ የተለያዩ ስጋቶችን የመለየትና በተቀናጀ አመራር ሥር የመፈጸም ብቃት ያስፈልገዋል።
ከዚህ በላይ የዘመናዊ መከላከያ ሠራዊት ተግባር ችግር ከተፈጠረ በኋላ ምላሽ መስጠት ብቻ አይደለም። ስጋትን አስቀድሞ መለየት፣ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር መገመትና ከመከሰቱ በፊት መግታት የዝግጁነት ዋነኛ መገለጫ ነው።
ችግሩ ቢፈጠርም ፈጣንና ተመጣጣኝ ምላሽ በመስጠት ሀገርን ከጉዳት መጠበቅ፣ ሁኔታው ከባድ ከሆነም የድል ችሎታን ማሳየት የሠራዊቱ ዋነኛ ተልዕኮ ነው።
ይህ የድል ችሎታ ከዘመናዊ መሣሪያና ቴክኖሎጂ ብቻ የሚመነጭ አይደለም። ከኢትዮጵያ የቆየ የጀግንነት፣ የመስዋዕትነትና የሀገር ክብር ታሪክ ጋር የተሳሰረ ነው።
አባቶች በከባድ ፈተናዎች ውስጥ ሀገርን የመጠበቅና ድል የማድረግ ታሪክ አስቀምጠዋል። የዛሬው ሠራዊትም ይህን የድል ባህል ከዘመናዊ ወታደራዊ አቅም ጋር በማጣመር የዘመኑን ፈተና መመከት የሚችል ኃይል ሆኖ መገንባት ይጠይቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት በተካሄደው አዲሱ የመደመር መንግሥት ምሥረታ ላይ የመከላከያ ሠራዊትን ግንባታ በተመለከተ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ የዓለምና የአካባቢውን ወቅታዊ ሁኔታ ብሎም የወደፊቱን የዓለም አካሄድ ያገናዘበ የመከላከያ ሠራዊት እንዲኖረን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በቀጣናችን የአየር የበላይነት ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ኢትዮጵያ ትገነባለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ሠራዊቱ ዘመናዊ፣ ሁሌም ዝግጁ፣ ብቁና ንቁ፣ እንዲሁም በየአውዶቹ የመሰማራት አቅምና ቁመና ያለው እንደሚሆን አብራርተዋል።
ሠራዊቱ ችግሮች ሳይፈጠሩ በፊት አስቀድሞ ማወቅና መግታት፣ ከመጡም መከላከል፣ ከባሰም እንደ አባቶቹ እንደ ልማዱ ማሸነፍ የሚችል ኃይል ሆኖ ይገነባል ነው ያሉት።
የመከላከያ ሠራዊት ግንባታ የሚለካው በዛሬ የውጊያ አቅሙ ብቻ ሳይሆን፣ ነገን በመገመት ራሱን የማዘጋጀት ብቃቱም ጭምር ነው።
ስጋትን አስቀድሞ ማወቅና መግታት፣ ችግር ሲከሰት በፍጥነት መመከት፣ ሁኔታው ከባድ ሲሆን ደግሞ እንደ አባቶቹ የድል ታሪክን መድገም የሚችል ኃይል መሆን የዚህ ግንባታ ዋነኛ ዓላማ ነው።
ዘመኑን የዋጀ መከላከያ ሠራዊት ሰላምን በመጠበቅ፣ ስጋቶችን በቅድሚያ በመለየት፣ ችግሮችን በፍጥነት በመመከትና አስፈላጊ ሲሆን ድልን በማረጋገጥ የሀገርን ሉዓላዊነት የሚያስከብር ኃይል ነው።
የአባቶችን የድል ቅርስ ከዘመናዊ እውቀትና ቴክኖሎጂ ጋር በማጣመር፣ ዘመኑን የሚመጥን፣ ሁሌም ዝግጁና ብቁ የመከላከያ ኃይል መገንባት የሀገር ሕልውናንና ሰላምን የማረጋገጥ ዋስትና ነው።
#የመደመር_መንግሥት
በመላኩ ገድፍ

