አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ድምጻዊው በዜማው እንዳንጎራጎረው ኢትዮጵያ ለጠላቶቿ ሁልጊዜም የማትገመት፣ የውድቀት ሳይሆን የመነሳትና የድል ታሪክ ብቻ ያላት ድንቅ ሀገር ናት።
ደከመች ሲሏት የምትጠነክር፣ ወደቀች ሲሏት ደግሞ በበለጠ ግርማ የምትነሳ ተዓምረኛ ምድር ናት።
በታሪኳ ሁሉ ጠላቶቿ ሊጥሏት፣ ሊበታትኗትና በውስጥ ተንኮል እርስ በእርስ ሊያባሏት ትናንትም ሞክረዋል፤ ዛሬም ቀጥለዋል።
ሆኖም ይህ ሁሉ ሴራና ፈተና አንድም ቀን ውድቀትን አላስከተለባትም፤ ይልቁንም ፈተናዎቹን እንደ እሳት መፈተኛ ተጥቀማ የባሰ ጠንክራና አሸንፋ እንድትወጣ አደረጓት እንጂ።
የታሪክ መዛግብት እንደሚመሰክሩት ኢትዮጵያ ነጻነቷንና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ስትል በርካታ የውጭ ወረራዎችንና ጥቃቶችን አስተናግዳለች።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን ግብፅ የዓባይን ወንዝ መነሻ ለመቆጣጠር ባደረገችው ተደጋጋሚ ሙከራ በአጼ ዮሐንስ 4ኛ መሪነት በህዳር 7/1868 ዓ.ም በጉንደት እንዲሁም በመጋቢት 7/1868 ዓ.ም በጉራ ጦርነቶች አሳፋሪ የሽንፈት ካባ ተከናንባ ተመልሳለች።
በተመሳሳይ በ1881 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ወረራ የፈጸሙት ደርቡሾች (የሱዳን ማህዲስቶች) በመተማ ጦርነት ድል ተነስተው ኢትዮጵያን የማፍረስ እኩይ ሴራቸው ከንቱ ሆኖ ቀርቷል።
በ1888 ዓ.ም ፋሺስት ጣሊያን ያደረገውን ትልቅ ወረራ በማክሸፍ፤ ኢትዮጵያ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነትና እንደ ሰው የመቆጠር ድል ምክንያት የሆነውን ታሪካዊ ዓድዋን በደሟ አውጃለች።
ኢትዮጵያ ያልተጋፈጠችው ጦርነት፤ ድል ያላደረገችው የጦርነት አውድ የለም። ሁሉንም እንደ አመጣጡ መክታ፤ መስመር አስይዛና አስተምራ መልሳለች።
በእነዚህ ሁሉ የወረራና የጦርነት ታሪኮች ውስጥ አንድም የኢትዮጵያ ውድቀት የተጻፈበት የታሪክ ገጽ የለም፤ የታወቀውና የተመዘገበው ድል አድራጊነቷ ብቻ ነው።
ዛሬም ቢሆን ፈታኞቿና ፈተናዎቿ አልቆሙም፤ የዛሬዎቹ ጠላቶቿ ታሪክ ያላስተማራቸው የትናንቶቹ ሰንካሎች፤ በውስጥ የሚያንቀሳቅሷቸው ደግሞ የትናንት ባንዳዎች የእፉኝት ልጆች ናቸው።
እንደ አረም ተጣብቀው ሀገር ለማጥፋትና ምርጥ ዘሯን በእንክርዳድ ለማበላሸት የሚጥሩ ብኩኖች ቢሆኑም፤ ውጤቱ ግን የትናንቱ ነው የሚሆነው።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጽናትና የማይበጠስ የጀግንነት ታሪክ እየተመራች፤ እንክርዳዶቹን እየነቀለች፣ ምርጥ ዘሯን እያበዛችና የጠላቶቿን የግፍ ግንብ እየደረመሰች ትልቅነቷን ወደ ታላቅነት በማሸጋገር ጉዞዋን በድል ትቀጥላለች!
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ #የመደመርመንግሥት
በታሪኩ ለገሰ

