Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካን ነገ ለመቀየር የሕጻናትን ጤና ማረጋገጥ ወሳኝ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካን ነገ ለመቀየር የሕጻናትን ጤና ማረጋገጥ ወሳኝ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡
የኢትዮጵያና ናይጄሪያ የሥርዓተ ምግብ አመራር የልምድ ልውውጥ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በስትራቴጂካዊ አጋርነት የተሣሠሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የሁለቱ ሀገራት ሰፊ የሕዝብ፣ የሰው ሀብትና የኢኮኖሚ ዐቅም በተቀናጀ ጥረት ሲመራ ለአፍሪካ ዕድገትና ብልጽግና ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
ናይጄሪያ በሰቆጣ ቃል ኪዳን ያመጣነውን ተጨባጭ ተሞክሮ ለመቅሰም ያደረገችው ጉብኝትም የዚህ አጋርነት ተጨባጭ መገለጫ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ሥርዓተ ምግብ የጤና ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የሰው ሀብት ልማት፣ የትምህርት ውጤት፣ የምርታማነት ዐቅምና የወደፊት ብልጽግና መሠረት መሆኑን አንስተዋል፡፡
የሥርዓተ ምግብ ጉዳይ በከፍተኛ የፖለቲካ አመራር፣ በተቀናጀ የመንግሥት ሥራና በተጠያቂነት መመራት ይገባዋል ነው ያሉት።
ባለፉት 10 ዓመታት በሰቆጣ ቃል ኪዳን የጀመረችውን ጉዞ በጠንካራ ፖለቲካዊ አመራር፣ በተቋማዊ አሠራር፣ በየደረጃው በሚደረግ ክትትልና በተቀናጀ የበጀት ምደባ በማስፋፋት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቧን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያና ናይጄሪያ የመሪዎች የልምድ ልውውጥ ይህን ተሞክሮ ከማካፈል ባለፈ የሁለቱን ሀገራት አቅም በማቀናጀት ለጤናማ፣ ምርታማና ብልፅግናዋን ለምታረጋግጥ አፍሪካ የጋራ መፍትሔ ለመፍጠር ዕድል እንደሚከፍት ጠቁመዋል።
የሕፃናት የዛሬ ጤና የአፍሪካ የነገ አቅም ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዚህ እምነት የሁለቱን ሀገራት ትብብርና የመሪዎችን ቁርጠኝነት በማጠናከር፣ ለጤናማና ምርታማ ትውልድ ጠንካራ መሠረት እንጥላለን ብለዋል።
Exit mobile version