Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለአፍሪካ የጋራ ብልጽግና ከሀገራቱ ጋር የሚሰሩት ቭላድሚር ፑቲን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ከሶቪየት ህብረት ዘመን የኬጂቢ የደህንነት ሥራ ጀምሮ እስከ ክሬምሊን ከፍተኛ ሥልጣን የደረሱት ፑቲን ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ በሩሲያ ፖለቲካ ማዕከል ውስጥ የዘለቁ መሪ ናቸው።
የፑቲንን ታሪክ ለመረዳት የአንድ ፕሬዚዳንትን የግል ታሪክ ብቻ መመልከት በቂ አይደለም። የሩሲያ የምጣኔ ሀብት ማደግ፣ የነዳጅና የጋዝ ሀብቷ በአውሮፓ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ፣ የሩሲያ ወታደራዊ ኃይል መጠናከር እና ከ2014 እስከ 2022 የተስፋፋው የዩክሬን ጦርነት ሁሉም በአንድ ሰንሰለት የተያያዙ ክስተቶች ናቸው።
በፈረንጆቹ 1952 በቀድሞዋ ሌኒንግራድ በዛሬዋ ሴንት ፒተርስበርግ የተወለዱት ፑቲን በሶቪየት የደህንነት ተቋም በሆነው ኬጂቢ ውስጥ ለዓመታት አገልግለዋል፡፡
ከዚያም በ1990ዎቹ ወደ ፖለቲካው ዓለም ሰተት ብለው ገቡ። በ1999 የሩሲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡ በኋላ በተከታዩ ዓመት የሩሲያ ፕሬዚዳንትነት መንበር ተቆናጠጡ።
የፑቲን የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን በአንድ በኩል ከ1990ዎቹ የሩሲያ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ የተለየ የመረጋጋት ዘመን ሆኖ ታየ።
ፑቲን ወደ ሥልጣን በመጡበት ዘመን የዓለም የነዳጅ ዋጋ መጨመር ለሩሲያ ትልቅ የገቢ ምንጭ ሆነ። የአይኤምኤፍ መረጃ እንደሚያሳየው በ2000 የሩሲያ ጥቅል ሀገራዊ ምርት እድገት 10 በመቶ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ከፍተኛ የኃይል ዋጋ ዕድገትም የመንግሥትን ገቢና የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ ለማሳደግ አግዟል።
ይህ ለሩሲያ በጣም ወሳኝ ነበር። በ1990ዎቹ የተዳከመችው ሩሲያ የመንግሥት ገቢዋን ማሳደግ፣ የውጭ እዳዋን መቀነስ እና ወታደራዊ ተቋሟን እንደገና ለማጠናከር ቻለች።
የሩሲያ ኢኮኖሚ በአሁኑ ጊዜ ከቀድሞው በተለየ መልኩ በማዕቀብና በጦርነት ጫና ውስጥ ቢሆንም፤ በ2025 የዓለም ባንክ መረጃ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርቷ ወደ 2 ነጥብ 59 ትሪሊየን ዶላር መድረሱን ያሳያል።
ፑቲን የሩሲያን ዓለም አቀፍ ሚና በኢኮኖሚ ብቻ አልገነቡም። የወታደራዊ ኃይል መልሶ ግንባታ የአጀንዳቸው ዋና ክፍል ነበር።
2008 በጆርጂያ፣ 2014 በክሬሚያ እና በ2022 በዩክሬን ግጭት የአውሮፓን የደህንነት ስርዓት በጥልቅ ለውጦታል። የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እንደሚለው፣ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በትራንስ-አትላንቲክ የደህንነት አካባቢን በብዙ አስርተ ዓመታት ውስጥ ከታዩት ከፍተኛ ለውጦች አንዱ እንዲሆን አስችሎታል።
ውጤቱም የሩሲያ ወታደራዊ ኃይል ብቻ መጠናከር አልነበረም፤ አውሮፓም የራሷን የመከላከያ አቅም እንድታሳድግ ግፊት ተፈጥሯል። ኔቶ በምሥራቃዊ ክንፉ ያለውን የወታደራዊ ዝግጁነት አሳድጓል፤ አዲስ የመከላከያ ዕቅዶችንም አጠናክሯል።
ለብዙ ዓመታት ሩሲያ በአውሮፓ ላይ ያላት ተፅዕኖ በተለይ በየተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ የተመሠረተ ነበር። አውሮፓ 45 በመቶ ጋዝ፣ 27 በመቶ ነዳጅ እንዲሁም 46 በመቶ የድንጋይ ከሰል የምትገዛው ከሩሲያ ነበር፡፡
በ2021 በአውሮፓ ህብረት የኃይል ምርቶች አስመጪነት የሩሲያ ድርሻ ከፍተኛ ነበር። ከዩክሬን ጦርነት በኋላ ግን ይህ ግንኙነት በፍጥነት ተቀይሯል።
ይህ የሚያሳየው የፑቲን ዘመን ትልቁ የጂኦፖለቲካ ትምህርት አንዱ ነው፤ የኢኮኖሚ እና የኃይል አቅርቦት የውጭ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ እና የድርድር አቅም ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ፑቲን በተለያዩ መንገዶች የሚገለጹ ጉምቱ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ በአንድ ቃል መግለጽ አይቻልም።
ከ1990ዎቹ የኢኮኖሚ ውድቀት በኋላ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንደገና እንዲነሳ ያገዙ እና የሩሲያን የወታደራዊ ኃይል እንደገና ያጠናከሩ መሪ ናቸው። በተመሳሳይ ጊዜ የእሳቸው የዩክሬን ፖሊሲ በአውሮፓ ከባድ የደህንነት ቀውስ፣ ሰፊ ማዕቀብ እና የአውሮፓ-ሩሲያ የኢኮኖሚ ግንኙነት መበጣጠስ ምክንያት የሆነ ፖሊሲን የተገበሩ ገጸ ብዙ ሰው ናቸው።
የፑቲን የ74 ዓመት የልደት በዓል የአንድ ፖለቲከኛ የሕይወት ዓመታትን ብቻ የሚያስታውስ ቀን አይደለም፡፡
ሩሲያ ከ1990ዎቹ ድክመት ወደ ዛሬው የዓለም ኃያል ሀገርነት የተጓዘችበትን መንገድ፣ እንዲሁም ይህ ጉዞ በአውሮፓ የወታደራዊ፣ የኢኮኖሚ እና የጂኦፖለቲካ ሚዛንን እንዴት እንደለወጠ የምንመለከትበት አጋጣሚ ነው።
የዛሬዋ ሩሲያ ከአውሮፓ ጋር በንግድ እጅግ የተለየች ብትሆንም፣ በወታደራዊ እና በደህንነት ጉዳይ የፈጠረችው ተፅዕኖ አሁንም ግዙፍ ነው።
የፑቲን ዘመን በአውሮፓ የሩሲያ ተፅዕኖ የጨመረበትንም ሆነ በተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ውስጥ በወታደራዊና ልማት ዘርፎች የነቃ ተሳትፎ ማድረግ የፑቲን አመራር ውጤት ናቸው።
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለአፍሪካ አዎንታዊ ምልከታ ያለቸው ሲሆን፤ ለጋራ ብልጽግና ከአህጉሪቱ ሀገራት ጋር በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ጋር ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከመፍጠርም ባለፈ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን የአንበሳውን ድርሻ መጫወታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በአቤል ነዋይ
Exit mobile version