አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) “ለውጥ የሕይወት ሕግ ነው፤ የትናንት እና የዛሬን ብቻ የሚመለከቱ ነገ ያመልጣቸዋል”፤ ይህን የተናገሩት፥ 35ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ናቸው፡፡
በዚህ ንግግር አውድ የኢትዮጵያን ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ ስንቃኝ፤ ሀገራችን ቁልፍ ሀብቶቿን ያጣችው ትናንት ላይ ሆነው ዛሬን ለማየት ባልታደሉ ገዢዎች ያልበሰሉ ውሳኔዎች ምክንያት መሆኑን በውል መገንዘብ ያስችለናል፡፡
እናም እነዚያ የኋሊት ብቻ እየተመለከቱ፤ የዕለት የዕለቱን ሲያዘግሙ የነበሩ ገዢዎቿ፤ ከሕዝብ ሳይማከሩ እንደ ዋዛ ባሳለፉት ውሳኔ ኢትዮጵያ ከባህር በሯ ተነጥላ ለዓመታት ተዘግታ ለመኖር ተገደደች፡፡
በሀገራቸው ጉዳይ እንደ ባይተዋር የተቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፤ መሻታቸው ሳይጠየቅ፤ ይሁንታቸውን ሳይገልጹ የባህር በራቸውን በመነጠቃቸው ለዘመናት ሲብሰለሰሉና፤ በቁጭት ሲብከነከኑ ኖረዋል፡፡
የባህር በር እጦት ከቁጭት ባሻገር የእያንዳንዱን ዜጋ በር ያንኳኳ፤ የሀገርን ኢኮኖሚ ክፉኛ የጎዳ ከፍተኛ ኪሳራ ያስከተለ ነው፡፡
ለአብነትም በተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ጉባኤ መረጃ መሰረት፤ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ቀጥተኛ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ከዓለም አማካይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ወጪ ከ50 በመቶ በላይ ተጨማሪ ወጪ ለማውጣት ይገደዳሉ፡፡
ይህ ወጪ እያንዳንዱ ዜጋ በሚሸምታቸው ሸቀጦች ዋጋ ላይ ሊንጸባረቅ የሚችል በመሆኑ በዜጎች ዕለታዊ የግዢ አቅም ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ማለት ነው፡፡
ሆኖም በትናንት ላይ ያልተቸከለው፤ በዛሬ ላይ ያልታጠረውና፤ መጪዎቹን ትውልዶች የሚያማትረው የመደመር መንግሥት፤ “ኢትዮጵያ ተዘግታ አትቀርም” በማለት ብቅ አለ፡፡
በዚህም የኢትዮጵያን ዘላቂ እድገት በሚፈለገው ፍጥነት ለማረጋገጥና ብሔራዊ ደህንነቷን ለማስጠበቅ የባህር በር የሕልውና ጉዳይ ነው የሚል የጋራ ሀገራዊ አጀንዳ መፍጠር ችሏል፡፡
ይህ ርምጃ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀውን የመብሰልሰል ምዕራፍ የከረቸመ፤ ኢትዮጵያ ህጋዊ እና ታሪካዊ እውነቷን ይዛ የባህር በሯን ማስመለስ እንደምትችል ከፍተኛ መተማመን የፈጠረ ጨዋታ ቀያሪ ድል ነው፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያውያን በባሕር በር ጉዳይ አይሽኮረመሙም፤ ለነገ የማይሉት ጊዜ የማይሰጥ የሕልውና ጉዳይ አድርገውታል፡፡
የመደመር መንግሥት፤ ይህንን የትውልዶች ጉዳይ ተቀዳሚ አጀንዳ ከማድረግ ተሻግሮ፤ ከሕዝቡ ጋር በመናበብ ተግባራዊነቱ ከየትኛውም ጊዜ በላይ እንዲቀርብ አድርጓል፡፡
ይህ መናበብ፤ ኢትዮጵያ ወደሚገባት ቦታ ትደርስ ዘንድ ሕዝብን የሚያደምጥ፤ ሕዝብም የሚያደምጠው መንግሥት ለማግኘቷ አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲሱ የመደመር መንግሥት ምስረታ ዕለት እንዳረጋገጡት፤ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያለ ባህር በር እውን ሊሆን አይችልም፡፡
እናም “ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ፤ ወጥቶ መግቢያ በር እንዲኖራት ተግተን እንሰራለን” በማለት፤ ኢትዮጵያን ዳግም የባህር በር ባለቤት የማድረግ ጉዞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ይህ ትውልድ በትናንት ስህተቶችና በዛሬ ፈተናዎች ላይ ተጠምዶ የነገው ትውልድ የሚገባውን ብልጽግና እንዳያጣ፤ ይህን ታሪካዊ ጉዞ ከግብ ማድረስ ይጠበቅበታል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

