አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአምስት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ተጫዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ ፖርቹጋል ከዴንማርክ ጋር ከምታደርገው የኔሽንስ ሊግ ጨዋታ በፊት የብሔራዊ ቡድኑን ካምፕ ለቅቆ በመውጣት መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ይህን ተከትሎ ከተነሳው ውዝግብ በኋላ ሮናልዶ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ጆርጌ ጄሱስ የገባልኝን ቃል አፍርሷል በማለት ወቅሷል፡፡
ሮናልዶ ትናንት ምሽት በማህበራዊ የትስስር ገጹ ባሰፈረው 1 ሺህ 740 ቃላት ርዝመት ባለው ጽሁፉ ባለፈው ሳምንት በነበሩት የኔሽንስ ሊግ ጨዋታዎች አጋማሽ ላይ ቡድኑን ጥሎ በመውጣቱ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።
ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የአውሮፓ ዋንጫንና የኔሸንስ ሊግን በማሸነፍ ስኬታማ ታሪክን መጻፍ የቻለው አምበል ለሀገሩ ደጋፊዎች እና ለቡድን አጋሮቹ ይቅርታ የጠየቀ ቢሆንም፣ ድርጊቱ የተቀሰቀሰው በአሰልጣኙ ምክንያት እና በጠበቀው ታማኝነት መሸርሸር መሆኑን አስምሮበታል።
ሮናልዶ ባሰፈረው ጽሁፍ መሠረት የችግሩ ዋነኛ መንስኤ ከኖርዌይ ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይ የተፈጠሩት ሁነቶች እንደሆኑ አንስቷል።
ሮናልዶ እንደገለጸው አሰልጣኙ በጨዋታው ላይ ለ30 ደቂቃዎች ያህል እንደሚያሰልፉት አስቀድሞ ስምምነት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፤ አሰልጣኙ ግን ቃላቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል።
አለመግባባቱ የበለጠ የከረረው ደግሞ ከጨዋታው በኋላ በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አሰልጣኙ አስቀድሞ በጋራ የተስማሙበትን ሀሳብ ብቻ ለማቅረብ የነበራቸውን ውል ጥሰው የተለየ መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ እንደሆነም አብራርቷል።
የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና አሰልጣኝ ጆርጌ ጄሱስ ለዚህ የሮናልዶ ከባድ ክስ በሚሰጡት ይፋዊ ምላሽ እና በሚወስዱት ርምጃ ላይ አሁንም የዓለም እግር ኳስ ቤተሰቦች በትኩረት የሚጠባበቁት ጉዳይ ሆኗል፡፡
ሮናልዶ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መልዕክትም ከብሔራዊ ቡድኑ ራሱን ለማግለል ጊዜው እንዳልደረሰም ጠቁሟል፡፡
በመልካም ፈቃዱ

