Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ክፍያና ብድርን የሚያሳልጥ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለማቅረብ ስምምነት ተፈረመ

ለ148 ሺ ነጋዴዎች የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት ማቅረብ የሚያስችል ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈርሟል፡፡

ስምምነቱን በዲጂታል ክፍያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነው ቪዛ እና የኢትዮጵያ የክፍያና ዲጂታል ባንክ መሠረተ ልማት ድርጅት የሆነው ኢታ ሶሉሽንስ ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት148 ሺህ የክፍያ መቀበያ መሳሪያዎች እና ዘመናዊ የሽያጭ መሳሪያ ተርሚናሎች ለአነስተኛና መካከለኛ ነጋዴዎች የሚሰራጩ ይሆናል፡፡

አገልግሎቱ በአዲስ አበባና በዋና ዋና የክልል ከተሞች ለሚገኙ ሱቆች፣ ገበያዎች፣ መድኃኒት ቤቶች፣ ምግብ ቤቶችና የትራንስፖርት አገልጋዮች ተደራሽ እንደሚያደርግ ተመላክቷል፡፡

መሣሪያዎቹ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ባገኘው ዞሪያ ፔይ ሥርዓት የሚሰሩ ሲሆን÷ በኢትዮጵያ ታክስ ባለስልጣንም እንደ ጥሬ ገንዘብ መመዝገቢያ ማሽን እውቅና ያገኙ ናቸው፡፡

ስምምነቱ የብድር እድል ማግኘት የሚያስችል ሲሆን ÷ ይህም በኤታ እና ኦፕታሲያ አጋርነት አማካይነት፣ ነጋዴዎች የሚያካሂዱት የዲጂታል ግብይት ታሪክ ታስቦ ያለ መያዣ እና ያለ ወረቀት ፕሮሰስ ከባንኮች የንግድ ማስፋፊያ ብድር እንዲያገኙ ዕድል ይፈጥርላቸዋል።

የኢታ ሶሉሽንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የ ዞርያ ፔይ ቦርድ ሰብሳቢ ተመስገን ገብረሕይወት (ዶ/ር) ÷ ስምምነቱ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

በሁለቱ ኩባንያዎች የጋራ ፋይናንስና ድጋፍ የሚካሄደው አገልግሎቱ ሥርጭቱ በአዲስ አበባ ተጀምሮ በቅርቡ ወደ ሁሉም ክልሎች እንደሚስፋፋ ተመልክቷል፡፡

 

Exit mobile version