Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሹመት ብዙ ኃላፊነት እና ድካም ያለው ጉዳይ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሹመት ብዙ ምቾት፣ ብዙ እንቅልፍ፣ ብዙ ድሎት ያለው ሳይሆን ብዙ ኃላፊነት እና ድካም ያለው ጉዳይ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 7ኛ የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ማካሄድ ጀምሯል፡፡
በመደበኛ ስብሰባው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔያቸውን እጩዎች አባላት ዝርዝር አቅርበው በምክር ቤቱ ፀድቋል።
በዚህም መሰረት ሹመኞች ብቁ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው መሆኑ ዋነኛ መስፈርት ቢሆንም ትምህርት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ጥሩ የመፈጸም አቅም ያላቸውን ሰዎች ከትምህርት ዝግጅታቸው ጋር ለማጣጣም ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
የተማረ ግን የማይፈጽም ከሆነ ለሚፈለገው ግብ ውጤት ማምጣት የማይችል መሆኑን በመጥቀስ በተሰማሩበት የሥራ መስክ የተሻለ አፈጻጸም ያላቸውን ሰዎች ለማካተት ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡
፡
የሚቀጥሉት 5 ዓመታት ብዙ መሮጥ እና መሥራት የሚያስፈልግበት በመሆኑ ይሄን ሩጫ መሮጥ የሚያስችል ብቃት ያላቸውን ሰዎች ከግንዛቤ ለማስገባት ተሞክሯል ነው ያሉት።
ከሁሉም በላይ በብዙ መከራ መንግሥት ለማጽናት ከ54 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን በምርጫ ድምጽ መስጠታቸውን አስታውሰው ይህንን በሚገባ የሚረዱ ሰዎች እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል ሲሉ አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም ሙስናን የሚጸየፉ እና ህዝብ የሚጠይቀውን አገልግሎት በሚገባ የሚከውኑ እንዲሆኑ ተሞክሯል፡፡
ኢትዮጵያ እስከ 2050 የሚዘልቅ የመደመር ግራንድ ስትራቴጂ ማዘጋጀቷን ጠቅሰው ይሄን ስትራቴጂ በቅጡ የሚረዱ በስትራቴጂው ውስጥ የተቀመጡ ዝርዝር እሳቤዎች የተገነዘቡ መሆናቸውን ከግንዛቤ ለማስገባት ተሞክሯል ብለዋል፡፡
ብቃት እና የብሔር ስብጥርን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን ጥረት መደረጉን አንስተዋል፡፡
ከምንም በላይ ሹመት ብዙ ምቾት፣ ብዙ እንቅልፍ፣ ብዙ ድሎት ያለው ሳይሆን ብዙ ኃላፊነት እና ድካም ያለው ጉዳይ መሆኑን በሚገባ የተረዱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
በአቤል ነዋይ
Exit mobile version